ሶስተኛው ዙር የመቀንጨር በሽታ ጥናት ሊካሄድ ነው

113
አዲስ አበባ ሀምሌ 10/2010 እናቶችና ህጻናትን መሰረት ያደረገ የመቀንጨር በሽታን ለመከላከል የሚያስችል ጥናት ለማካሄድ አላይቭ ኤንድ ትራይቭ ኢትዮጵያ የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት 3ኛ ዙር ፕሮጀክቱን ዛሬ ይፋ አድርጓል። የመቀንጨር በሽታ የሚከሰተው በአመጋገብ ስርዓት መዛባት የሚመጣ ነው። በድርጅቱ የስነ ምግብ ባለሙያው ዶክተር አብዱላዚዝ አሊ እንደተናገሩት፤ ከዚህ ፕሮጀክት ቀደም ብሎ የተካሄዱት ሁለት ዙር ጥናቶች ህጻናትና ጨቅላ ህጻናት ላይ ብቻ በማተኮራቸው ውጤቱ በሚፈለገው ልክ ባለመሆኑ እናቶችንና ወጣቶችን ማካተት አስፈልጓል። በአማራ፣ ትግራይ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ፣ አፋርና ሶማሌ ክልሎች ላይ ጥናቱ እንደሚካሄድ የገለጹት ባለሙያው “ህጻናትን ከመቀንጨር በሽታ ለመከላከል በቅድሚያ የእናቶችን የአመጋገብ ስርዓት ማስተካከልና ማረጋገጥ ተገቢ ነው'' ብለዋል። በአገር አቀፍ ደረጃ 25 በመቶ የሚሆኑት እናቶች የመቀንጨር በሽታ ተጠቂዎች በመሆናቸው ጥናቱን ለማካሄድ ምክንያት መሆኑንም ጠቁመዋል። ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና ከግብርናና ከእንስሳት ኃብት ልማት ሚኒስቴር ጋር በመሆን ጥናቱን ሊደግፉ በሚችሉ ዋና ዋና ተግባራት ላይ ስምምነት መደረጉንም ዶክተር አብዱላዚዝ አክለዋል። ጥናቱ በስነ-ምግብና በጤናው ዘርፍ ያሉ ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት መፍትሄ አመላካች እንዲሆን ያለመ መሆኑንም ጠቁመዋል። በድርጅቱ የስርአተ ምግብ ባለሙያና የፕሮጀክቱን መነሻ ሃሳብ ያቀረቡት ዶክተር የውልሰው አበበ በ1ኛና በ2ኛው ዙር የተካሄዱ ጥናቶች እናቶችንና ወጣቶችን ሳያካትቱ በህጻናትና ጨቅላ ህጻናት ላይ ብቻ የተወሰኑ እንደነበር አስታውሰዋል። በዚህም የመጀመሪያው ዙር ጥናት  እኤአ  ከ2009-2014 በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ትግራይና ደቡብ ክልሎች በህጻናት ላይ ብቻ በማተኮር መከናወኑን ጠቅሰዋል። ጥናቱም ከክልሎቹ የጤና ቢሮዎች ጋር በመቀናጀት፤ በዋናነትም ከህጻናት አመጋገብና የጡት ምግብን በማሻሻል ላይ ትኩረት በማድረግ የተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል። በ2ኛው ዙር በአማራ ክልል ብቻ ተወስኖ የተካሄደው ጥናት ህጻናት ላይ በማተኮር የተሰራው ጥናት ክልሉ የተሻለ የምግብ ሰብል አምራች ቢሆንም የህጻናት እድገት ውስንነት መኖሩን የሚያመላክት ውጤት እንደተገኘ አስታውሰዋል። 3ኛውን ዙር ጥናት ለማካሄድ በ1ኛውና በ2ኛው ዙር የነበሩ ጠንካራና ደካማ ጎኖች ተለይተዋል። በዚህም የተለዩትን ጠንካራና ደካማ ጎኖች መነሻ በማድረግ 3ኛውን ዙር እናቶችንና ህጻናትን ተሳታፊ በማድረግና ከዚህ በፊት በፕሮግራሙ ያልተካተቱ ክልሎችንም በማካተት እንደሚካሄድ ዶክተር የውልሰው ጠቁመዋል። የግብርናና እንስሳት ኃብት ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ እያሱ አብረሃ በበኩላቸው “በቂ የስነ-ምግብ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ትርፍ ለማምረት በትኩረት ይሰራል'' ብለዋል። በተለይም የስንዴ ምርት ፍላጎት 9 በመቶ ሲሆን የሚመረተው ደግሞ 7 በመቶ ብቻ መሆኑ ፍላጎቱና ምርቱ ተመጣጣኝ እንዳይሆን ማድረጉን ገልጸዋል። የስንዴ ፍላጎት መጨመሩን ተከትሎ አርሶ አደሩ ትርፍ ምርት ማምረት ላይ ግንዛቤው እንዲያዳብር የሚሰራው ስራ በቂ ባለመሆኑ ምርት መጨመር ላይም ሆነ የህጻናትና የእናቶች መቀንጨር በሽታ ለመግታት ከተባባሪ አካላት ጋር ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል። በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የስነ-ምግብ ጥናት አስተባባሪ አቶ ቢራራ መለስ በአሁኑ ወቅት እየተቀዛቀዘ የመጣው የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም በማጠናከር የአመጋገብ ስርዓት ላይ በስፋት በመስራት ችግሩን ለመከላከል ይሰራል ብለዋል። በዚህም አሰራሩን በድጋሚ እንዲያንሰራራ በማድረግ እናቶችና ህጻናትን ከመቀንጨር ለመታደግ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በትኩረት ይሰራል ብለዋል። 3ኛውን ዙር የእናቶችንና የወጣቶችን መቀንጨር ለመግታት ለሚካሄደው ጥናትም 15 ሚሊዮን ብር ተበጅቷል።                            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም