ኢንጂነር ታከለ ኡማ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ በመሆን ተሾሙ

74
አዲስ አበባ ሀምሌ 10/2010 የመዲናዋ ምክትል ከንቲባ በመሆን የተሾሙት ኢንጂነር ታከለ ኡማ የከንቲባነት ሙሉ ኃላፊነት ወስደው እንደሚያገለግሉ ታውቋል። ይህ ሊሆን የቻለው ኢንጅነር ታከለ የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባል ባለመሆናቸው በመሆኑ ነው ተብሏል። የከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 5ኛ አስቸኳይ ጉባኤው፤ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተሻሻለው አዋጅ መሰረት ነው ምክትል ከንቲባውን የሾመው። ከንቲባ ድሪባ ኩማ ለከንቲባነት ከተሾሙበት ከ2005 እስከ ሰኔ 30 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ በኃላፊነት የቆዩ ሲሆን አሁን ላይ በአምባሳደርነት ተሹመዋል። ኢንጂነር ታከለ ኡማ አሁን ላይ የኦሮሚያ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ሆነው እያገለገሉ ነበር። ከዚህ ቀደም የኦሮሚያ የከተማ መሬት ዘርፍ ዋና ስራ አስኪያጅ፣ የሆፕ 2020 ስራ አስኪያጅ፣ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ የከተማ አመራርነት፣ የሆለታ ከተማ ከንቲባ እነዲሁም የሰበታ ከተማ ኢንዱስትሪና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ በመሆንም በአጠቃላይ ለ11 ዓመታት በአመራርነት አገልግለዋል። በተጨማሪም በተለያዩ በጎ አድራጎት ድርጅቶች በኃላፊነት ሰርተዋል። የትምህርት ዝግጅታቸው የመጀመሪያ ዲግሪ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኬሚካል ኢንጅነሪግ የያዙ ሲሆን ከተመሳሳይ የትምህርት ተቋም በዋተር ሰፕላይና ኢንቫይሮመንታል ኢንጂነሪንግ ሁለተኛ ዲግሪ አግኝተዋል። አዲስ አበባ ከ1902 ዓ.ም ጀምሮ በከንቲባ መመራት የጀመረች ሲሆን ከቢትወደድ ወልደፃድቅ ጎሹ እስከ አዲሱ ተሿሚ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ድረስ 31 ከንቲባዎች ተሹመዋል። ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለም በምክር ቤቱ ፊት ቃለ መኃላ የፈጸሙ ሲሆን፤ የከንቲባውን ሙሉ ኃላፊነት ወስደው ያገለግላሉ። ምክር ቤቱ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስና ዶክተር ሰለሞን ኪዳኔን በምክትል ከንቲባነት ሹሟል። በተመሳሳይ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የተፋሰስና አረንጓዴ አካባቢዎች ኤጀንሲ ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅን አጽድቋል። በጉባኤው የፀደቀው አዋጅ ቁጥር 61/2010 አረንጓዴ አካባቢዎችን ለማስፋትና ለመጠበቅ፣ የውሃ ብክለት ለመከላከልና የከተማዋን መልካም ገፅታ ለመገንባት የተዘጋጀ እንደሆነም ተገልጿል። በአዋጁ መሰረት ከዚህ በፊት የዘላቂ ማረፊያ፣ ውበትና ፅዳት አስተዳደር ኤጀንሲ ተብሎ የሚጠራው መስሪያ ቤት አሁን በሚቋቋመው ኤጀንሲ ስር እንደሚጠቃለል ነው የተገለፀው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም