የቱሪዝም ሀብቶችን ማስተዋወቅ ዓላማው ያደረገ የተራራ ላይ የብስክሌት ጉዞ ሊካሄድ ነው

አዲስ አበባ ህዳር 4/2013 (ኢዜአ) በስምጥ ሸለቆ አካባቢ የሚገኙ ድንቅ የቱሪዝም ሀብቶችን ማስተዋወቅ ዓላማው ያደረገ የተራራ ላይ የብስክሌት ጉዞ ሊካሄድ መሆኑን ቱሪዝም ኢትዮጵያ አስታወቀ።

የቱሪዝም ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ግርማ ጉዞውን አስመልክተው ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመጪው ህዳር 11 ቀን 2013 ዓ.ም የሚጀምረው የተራራ ላይ የብስክሌት ጉዞ 30 ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚሸፍን ሲሆን ከግል ባለሀብቶች ጋር በመተባበር የሚዘጋጅ መሆኑ ተናግረዋል።

"የጉዞ ዓላማ በኢትዮጵያ የብስክሌት ጉብኝትን ማስተዋወቅ እና በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ተጎጂ የሆኑ የቱሪዝም አገልግሎት ሰጪዎችን መደገፍ ነው" ብለዋል፡፡

የአገር ውስጥ ቱሪዝምን እና የጉዞ ቱሪዝምን ማበረታት ሌላው የጉዞው ዓላማ እንደሆነም ገልጸዋል።

በጉዞው ከአስር በላይ አገሮችን የሚወክሉ ከስልሳ በላይ የሚሆኑ ተሳታፊዎች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ዓለም አቀፍ ተቋማትን የሚወክሉ ዲፕሎማቶችና የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችም በጉዞው እንደሚሳተፉ ተመልክቷል፡፡

በብስክሌት ጉዞው ላይ ለሚሳተፉ ግለሰቦች የተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የተለያዩ ማበረታቻዎችን በሽልማት መለክ እንደሚሰጡም አቶ ስለሺ ተናግረዋል።

"በስምጥ ሸለቆ አካባቢ የሚገኙ ድንቅ የቱሪዝም ሀብቶች በተለይ የፍል ውሃ የቱሪዝም ጸጋዎች ለገበያ ሳይውሉ ቆይተዋል፤ በዚህ የተራራ ላይ የብስክሌት ጉዞም እነዚህ የቱሪስት መስህቦች በስፋት ይጎበኛሉ" ብለዋል፡፡


አቶ ስለሺ እንዳሉት የብስክሌት ጉዞው በኢትዮጵያ ውስጥ በደንብ ያልተሰራበትን የስምጥ ሸለቆ አካባቢ በተለይ ከአፋር፣ አዋሽ ጀምሮ እስከ አንኮበር ከተማ የቀድሞ የአፄ ምንሊክ ቤተመንግስትን የሚያካትት ነው።

ጉዞውን ቱሪዝም ኢትዮጵያ ከተስፋ ቱር፣ ከሰሜን ኤኮ ቱር፣ ከዳይናስቲ ኢትዮጵያ ቱር እንዲሁም ከኢትዮ ሳይክሊንግ ሆሊደይስ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው መሆኑ ታውቋል።

"ጉዞ ወደ ተራራ አናት" የሚል መጠሪያ የተሰጠው ይህ ጉዞ ፣ ተራራ ለመውጣት የሚወዱ ሰዎችን ለማሳተፍ ክፍት መሆኑም ተነግሯል፡፡

በቱሪስት መዳረሻዎች አምቡላንስን ጨምሮ የጎብኚዎችን ደህንነት ለመጠበቅ የሚያስችሉ ሥራዎች አስቀድመው እንደሚከናወኑም በመግለጫው ተመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም