ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት አምስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታወቀ

67

ሐረር፣ ህዳር 4 /2013(ኢዜአ) ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ያለውን አጋርነት ለመግለጽ አምስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለማድረግ መወሰኑን አስታወቀ። 

የዩኒቨርሲቲው መምህራንና ሠራተኞች በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ዙሪያ ዛሬ ውይይት አካሂደዋል።

በውይይት መድረኩ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ጀማል ዩሱፍ እንደገለጹት የሀገር መከላከያ ሠራዊትን በየአቅጣጫው ድጋፍ ማድረግ የሚያስፈልግበት ወቅት ነው።


እኛም  የምንችለውን ሁሉ ድጋፍ በማድረግ ለሠራዊቱ አጋርነታችንን በተግባር ማሳየት ይገባናል ብለዋል።

የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር የአምስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለማድረግ መወሰኑን አስታውቀዋል።

በውይይቱ የተሳተፉ የዩኒቨርሲቲው መምህራንና ሠራተኞችም ለሀገር ክብርና የህግ የበላይነትን ለማስከበር እየተዋደቀ ለሚገኘው ለጀግናው የመከላከያ ሠራዊት ከደመወዛቸው ቆርጠው ድጋፍ ለማድረግ ወስነዋል።

በተጨማሪ "ደሜን ለሀገሬ መከላከያ ሠራዊት" በሚል መሪ ሀሳብ ደም መለገሳቸውንም የዩኒቨርሲቲው የአለም አቀፍና የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አለምእሸት ተሾመ  ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም