የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ከ50 ሺ በላይ መምህራንና የትምህርት አመራር አባላትን የሙያ ብቃት ሊመዝን ነው

3816

አዲስ አበባ ግንቦት 3/2010 የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ በያዝነው ወር ከ50 ሺ በላይ ለሚሆኑ መምህራንና የትምህርት አመራር አባላት የሙያ ብቃት ምዘና እንደሚሰጥ አስታወቀ።

ምክትል የቢሮ ኃላፊ አቶ ማሞ ቦጋለ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፤ ለመምህራኑ በግንቦት 11 እና 12 ቀን 2010 ዓ.ም ምዘናው ይሰጣል።

መምህራን በሚያስተምሩት የትምህርት ዓይነት ላይ በቂ እውቀትና የማስተማር ክህሎት እንዲሁም የሙያው ስነ ምግባር ሊኖራቸው እንደሚገባ ጠቁመው፤ ምዘናው የሚካሄደው ብቁ ለሆኑ መምህራን እውቅና ለመስጠት፣ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥና የሙያ  ክፍተት ያለባቸው መምህራንን በየጊዜው ሙያቸውን እንዲያሳድጉ ለማድረግ መሆኑን ገልፀዋል።

ከቅድመ መደበኛ እስከ መሰናዶ ትምህርት ቤቶች የሚያስተምሩ ከመለስተኛ መምህራን ወይም ከሁለት ዓመት በላይ ሲያስተምሩ የነበሩና ፈቃደኛ የሆኑ መምህራን ለምዘና እንደሚቀርቡም አብራርተዋል።

ለዚህም ከ42 ሺህ በላይ የመጀመሪያ ደረጃና ሁለተኛ ደረጃ መምህራን እንዲሁም ከ8ሺ 800 በላይ የትምህርት ቤት አመራር አባላትም ለምዘናው መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

ለዚህ ተግባርም የምዘና ጣቢያዎች እንዲሁም ምዘናውን የሚያስፈፅሙ ባለሙያዎች ዝግጅታቸውን እንዳጠናቀቁ ነው የገለፁት።

አጠቃላይ የመምህራን ምዘና በትምህርት እውቀትና በማስተማር ዘዴ የሚለካ ሲሆን፤ የትምህርታዊ እውቀት 80 በመቶ ድርሻ እንዲሁም መምህራኑ ሲያከናውኑ የነበረው ማህደረ ተግባር ወይም ፖርቶ ፎሊዮ 20 በመቶ የሚሸፍን መሆኑ ተገልጿል።

ምዘናው አሁን እየተሰጠ ያለው በመንግስት ትምህርት ቤት ቢሆንም ወደ ፊት የግል ትምህርት ቤት አመራር አባላትንና መምህራንም ምዘና እንደሚሰጥ ገልፀዋል።