ኢንጂነር ታከለ ኡማ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ በመሆን ተሾሙ

241
አዲስ አበባ ሀምሌ 10/2010  የከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 5ኛ አስቸኳይ ጉባኤው፤ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተሻሻለው አዋጅ መሰረት ነው ምክትል ከንቲባውን የሾመው። ከንቲባ ድሪባ ኩማ ለከንቲባነት ከተሾሙበት ከ2005 እስከ ሰኔ 30 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ በኃላፊነት የቆዩ ሲሆን አሁን ላይ በአምባሳደርነት ተሹመዋል። ኢንጂነር ታከለ ኡማ  እስከአሁን  የኦሮሚያ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ሆነው እያገለገሉ ናቸው። ከዚህ ቀደም የኦሮሚያ የከተማ መሬት ዘርፍ ዋና ስራ አስኪያጅ፣ የሆፕ 2020 ስራ አስኪያጅ፣ በተለያዩ የኦሮሚያ ክልሎች የከተማ አመራር፣ የሆለታ ከተማ ከንቲባ፣ የሰበታ ከተማ ኢንዱስትሪና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ በመሆንም በአጠቃላይ ለ11 አመታት በአመራርነት አገልግለዋል። በተጨማሪም በተለያዩ በጎ አድራጎት ድርጅቶች በኃላፊነት ሰርተዋል። የትምህርት ዝግጅታቸው የመጀመሪያ ዲግሪ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኬሚካል ኢንጅነሪግ የያዙ ሲሆን ከተመሳሳይ የትምህርት ተቋም በወተር ሰፕላይና ኢንቫይሮመንታል ኢንጂነሪንግ ሁለተኛ ዲግሪ አግኝተዋል። አዲስ አበባ ከ1902 ዓ.ም ጀምሮ በከንቲባ መመራት የጀመረች ሲሆን ከቢትወደድ ወልደፃድቅ ጎሹ እስከ አዲሱ ተሿሚ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ድረስ 31 ከንቲባዎች ተሹመዋል። ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለም በምክር ቤቱ ፊት ቃለ መኃላ የፈጸሙ ሲሆን፤ የከንቲባውን ሙሉ ኃላፊነት ወስደው ያገለግላሉ። ምክር ቤቱ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስና ዶክተር ሰለሞን ኪዳኔን በምክትል ከንቲባነት ሹሟል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም