ከምዕራብ ጉጂ ዞን የተወጣጡ 375 ወጣቶችን በሰላም አምባሳደርነት ሰልጥነው ተመረቁ

130

ዲላ ህዳር 3/2013 (ኢዜአ) የካቶሊክ ቤተ -ክርሲቲያን እርዳታ ድርጅት ከምዕራብ ጉጂ ዞን አምስት ወረዳዎች የተወጣጡ 375 ወጣቶችን በሰላም አምባሳደርነት አሰልጥኖ አስመረቀ።

በድርጅቱ የሰላም ግንባታ አማካሪ ሳምራዊት ጥበቡ እንዳሉት ወጣቶቹ  ለአስር ቀናት የተሰጠውን ስልጠና በመከታተል  ያጠናቁ ናቸው።

ስልጠናው  ያተኮረው በሰላም ግንባታና በግጭት አፈታት ዙሪያ መሆኑን አመልክተው ይህም የአካባቢው ሰላም ዘላቂነቱ እንዲጠበቅ የወጣቶችን ተሳትፎ ለማጎልበት እንደሚያግዝ አስረድተዋል።

ቤተ ክርሲቲያኗ ከአጋር አካላት ጋር በመሆን በምዕራብ ጉጂና ጌዴኦ ዞኖች በልማትና በሰላም ግንባታ የተለያዩ ተግባራትን ስታከናውን መቆየቷንም ጠቅሰዋል።

የገላና ወረዳ ነዋሪዋ ወጣት ብርቱካን  ታደሰ የወሰደችው ስልጠና የሰላም አባሳደርነት ስራዋን በብቃት እንድትወጣ የሚያግዛት መሆኑን ገልጻለች።

ግጭትን የችግር መፍቻ አድርጎ የመውሰድ የተሳሳተ ዝንባሌን ለማስተካከል የበኩሏን ጥረት እንደምታደርግ ተናግራለች።

ወጣቶች የአሸባሪው የሸኔ ቡዱን አጀንዳ ተሽካሚ እንዳይሆኑ እንዲሁም ከአጎራባች ህዝቦች ጋር አሁን ያለው ሰላም ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሰላም አባሳደር ሚናዋን ለመወጣት ዝግጁ መሆኗንም  አስታውቃለች።

ወጣቶች ለጸብና ግጭት ከሚያነሳሱ ተግባራት እንዲርቁ ብሎም  የአካባቢያቸውን ሰላም ጠባቂ እንዲሆኑ የበኩሉን እየተወጣ መሆኑን የተናገረው ደግሞ የአባያ ወረዳ ነዋሪ  ወጣት ገለታ ገላን ነው።

ወጣቶች ሰራ ፈጣሪ እንዲሆኑ በዙሪያቸው ያሉ ምቹ ሁኔታዎችን በማመላከቱ ረገድ ከስልጠና ግንዛቤ መግኘቱን ተናግሯል።

የአባያ ወረዳ ጸጥታ ጽህፈት ቤት የአጎራባች ቀበሌዎች ሰላም ዘርፍ  ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ኃሌኬ በየአካባቢው የሚፈጠሩ የሰላም መታወክ ችግሮችን ለማስወገድ  የወጣቶች ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ወጣቱ ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት አካባቢውን በንቃት መጠበቅ ባለበት ወቅት ወጣቶቹ  በሰላም አምባሳደርነት ተሰይመው መመረቃቸው የጎላ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም