የህወሓት ጁንታ ቡድን በአዲስ አበባ ትርምስ እንዲፈጥሩ ያሰማራቸው 242 ሰዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

85

አዲስ አበባ ህዳር 3/2013 (ኢዜአ) የህወሓት ጁንታ ቡድን በአዲስ አበባ ትርምስ ለመፍጠር ያሰማራቸውን 242 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ማዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

በቁጥጥር ስር የዋሉት ግለሰቦች ከከሃዲው የሕወሓት ቡድን ተልዕኮ ወስደው ባለፉት አምስት ቀናት በአዲስ አበባ የተለያዩ ጥፋቶችን ለማድረስ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ መሆናቸውን ኮሚሽኑ አስታውቋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው በወቅታዊ ጉዳይ ላይ በሰጡት መግለጫ የሕወሓት ዘራፊ ቡድን በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ከፈፀመ በኋላ አዲስ አበባን ኢላማ ያደረገ ጥቃትና ትርምስ እንዲፈጠር ሲሰራ እንደነበር ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ የቡድኑን የጥፋት ተልዕኮ መነሻ በማድረግ ከኅብረተሰቡና ከተለያዩ የፀጥታ ተቋማት ጋር በመሆን ዓላማውን ለማክሸፍ መስራቱን ተናግረዋል።

በሕዝብ ጥቆማ እንዲሁም ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከደህንነትና ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመሆን ባደረገው ፍተሻና ብርበራ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችና ቁሳቁስ በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገልፀዋል።

ይህን የጥፋት አጀንዳ ለማስፈፀም የህወሃት ጁንታ ያሰማራቸው 242 ግለሰቦች በአዲስ አበባ ትርምስ ለመፍጠር ሲንቀሳቀሱ ተደርሶባቸው በቁጥጥር ስር እንደዋሉም አስታውቀዋል።

ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር ሲውሉ ቦምብ፣ ፈንጂ፣ ላውንቸርና የተለያዩ ተተኳሽ ጥይቶችም ተገኝተውባቸዋል ነው ያሉት።

18 ቦምብ፣ 2 ፈንጂ፣ 1 ፀረ ተሽከርካሪ፣ 1 ቻይና ሰራሽ ፈንጂ፣ 97 የእጅ ሬዲዮና ከሱር ኮንስትራክሽን ደግሞ 23 የረጅም ርቀት መገናኛ ሬዲዮ በምርመራ መያዙንም አክለዋል።

በግለሰቦችና በተቋማት ተከማችተው የተገኙ 130 መሳሪያዎች መያዛቸውንና 2 ሺህ 686 የክላሽ ጥይት፣ 1 ሺህ 942 የሽጉጥ ጥይት፣ አራት የጦር ሜዳ መነጽርና አንድ ላውንቸር መያዛቸውንም አብራርተዋል።

እንደ ኮሚሽነሩ ገለፃ፤ አንድ ጂፒኤስ፣ 744 የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች ከ4 ሺህ 626 ጥይቶች ጋር፤ ስድስት ህገወጥ የውጭ ስልክ መጥለፊያን ጨምሮ 31 ባለ አንቴና ቻርጀር በቁጥጥር ስር ውለዋል።

በሌላ በኩል 157 ሲም ካርድና 74 የፀጥታ የደንብ ልብሶችን ጨምሮ የአንድ ግለሰብ የተለያዩ የባንክ ደብተሮችና ሰባት ፓስፖርቶች ተገኝተዋል።

በቁጥጥር ስር የዋሉት የጁንታው ቡድን አባላት 208 የክስ መዝገብ እንደተደራጀባቸውና 620 የሰው፣ የሰነድ እንዲሁም የቴክኒክ ማስረጃ እንደተገኘባቸውም አብራርተዋል።

697Muse Mele and 696 others19 Comments89 SharesLikeCommentShare

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም