ሠራዊቱ ከሁመራ ሽራሮ መስመር በጥፋት ቡድኑ ላይ ጥቃት በመሰንዘር በርካታ ቦታዎችን እየተቆጣጠረ ነው - የአገር መከላከያ

አዲስ አበባ ህዳር 2/2013 (ኢዜአ) የአገር መከላከያ ሠራዊት ከሁመራ ሽራሮ መስመር በጥፋት ቡድኑ ላይ በከፍተኛ ፍጥነት ጥቃት በመሰንዘር በርካታ ቦታዎችን እየተቆጣጠረ መሆኑን አስታወቀ። 

በተለያዩ ግንባሮች እየተካሄደ ባለው ዘመቻ የጠላት ሃይል እያፈገፈገ መሆኑንም ገልጿል።

የመከላከያ ሠራዊት የኢንዶክትሪኔሽን ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል መሐመድ ተሰማ ከትናንት ከሠዓት ጀምሮ ባሉት 24 ሠዓታት ውስጥ ስለተከናወኑ ስራዎች መግለጫ ሰጥተዋል።

ሠራዊቱ እያከናወነ ባለው የዘመቻ ስራ እስካሁን አብዛኛውን የምዕራብ ትግራይ ክፍል መቆጣጠሩን ሜጀር ጄኔራል መሐመድ ገልጸዋል።

የምዕራብ ትግራይ ዘመቻ አካል የሆነው ከማይካድራ እስከ ሁመራ ያሉ ስትራቴጂክ ቦታዎችና ዋናውን መስመር በማጥቃትና በመቆጣጠር ሁመራና አካባቢው ከ"ጁንታው ሃይል" ተላቆ በሠራዊቱ ቁጥጥር ስር ይገኛል ብለዋል።

አሁን የመከላከያ ሠራዊት ከሁመራ እስከ ሽራሮ ባለው መስመር በከፍተኛ ፍጥነት በማጥቃት ላይ እንደሚገኝና ኢላማውም "ነውጠኛው የህዋሃት ቡድን" መሆኑን ገልጸዋል።

በዚሁ ግንባር በተካሄደው ዘመቻ በርካታ ቦታዎች፣ ንብረቶችና በርካታ ሰዎች እየተያዙ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በሌሎች ግንባሮች እየተካሄደ ባለው ህግ የማስከበር ዘመቻ መከላከያ ሠራዊቱ እያደረሰ ባለው ጥቃት የጠላት ሃይል ወደኋላ እያፈገፈገ ነው ብለዋል።

የአገር መከላከያ ሠራዊቱ በገባባቸው ቦታዎች ሁሉ የሚኖረው የትግራይ ሕዝብ ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገለት መሆኑንም ገልፀዋል።

ከሁመራ እስከ ጉዲ ያለው መስመር በሁመራ አካባቢዎች አጥፊው ሃይል ለረጅም ጊዜ ምሽግ ሲያዘጋጅ ሕዝቡን ሲያሰቃይና የልማት ስራዎችን ሲያስተጓጉል ነበር ብለዋል።

በተጠቀሱት አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸውም ተናግረዋል።

ዜጎቹን መርዳት የሚፈልጉ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር ተነጋግረው ወደ ቦታው በመሄድ ድጋፍ ማድረግ እንደሚችሉ ሜጀር ጄኔራል መሐመድ አመልክተዋል።

"ነውጠኛው የህወሃት ቡድን" የተለደመውን ቅጥፈቱን ትቶ ሽንፈቱን በጸጋ መቀበል አለበት ያሉት ሜጀር ጄኔራል መሐመድ "የአየር ሃይል የጦር ጀት ጥለናል፣ የኤርትራ ወታደር መጥቶ አብሮ ወግቶኛል" በሚል የሀሰት ፕሮፓጋንዳ በመንዛት ሽንፈቱን ላለመቀበል ምክንያት እየፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።

የህወሓት ጁንታ የኤርትራን መከላከያ ሠራዊት መለዮ ለታጣቂዎች በማልበስ ኤርትራ እንደወረረችው በመግለጽ ሕዝቡን እያደናገረ እንደሆነም ጠቁመዋል።

ቡድኑ ይህም ሳይበቃው ያስታጠቃቸው ሃይሎች እየተሸነፉ መሆኑን ሲያውቅ ያለበሰውን ሬንጀር በማስወለቅ በአሮጌ ጫማና በባዶ እግራቸው እንዲዋጉ በማድረግ ሠራዊቱ ንጹሃን ዜጎችን እየተዋጋ ነው የሚል የተለመደ ቅጥፈቱን እያስተላለፈ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

የመከላከያ ሠራዊትና የአየር ሃይሉ ኢላማዎች የጥፋት ቡድኑ ታጣቂዎች እንደሆኑና ከጁንታው ቡድን ተላቀው እጃቸውን እየሰጡ እንደሆነ ገልፀው ታጣቂዎች የእኩይ አላማ ሰለባ እንዳይሆኑ ትጥቃቸውን ፈተው መከላከያ ሠራዊቱን እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የትግራይ ሕዝብ የአጥፊው ቡድን ሰላባ ባለመሆንና የጥፋት ሃይሉ የመላው ኢትዮጵያ ጠላት መሆኑን አውቆ ከአገር መከላከያ ሠራዊቱ ጎን መቆም እንዳለበትም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም