የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ከወገንተኝነት የፀዳ ተቋም ለመሆን እየሰራ እንደሆነ ገለጸ

113
አዲስ አበባ ሐምሌ 10/2010 ከየትኛውም የፖለቲካ ወገንተኝነት በመጽዳት የአገርንና ህዝብ ደህንነት ለመጠበቅ የሚያስችሉ የለውጥ ስራዎች እየሰራ መሆኑን የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ገለፀ። የተቋሙ አመራሮች “ተቋማችንን የሚፈራ ሳይሆን የሚከበር ለማድረግ ተግተን እንሰራለን'' በሚል መሪ ሀሳብ ከአባላቱ ጋር በተቋሙ ለውጥ ዙሪያ እየተወያዩ ነው። የተቋሙ ዳይሬክተር ጄኔራል አደም መሀመድ ውይይቱን በንግግር ሲከፍቱ እንደተናገሩት፤ ተቋሙ የአገሪቱን ብሄራዊ ጥቅም፣ የህዝቦችን ደህንነት፣ የአገሪቱን ኢኮኖሚ አደጋ ላይ እንዳይወድቅ ለመከላከል ይሰራል። ፈጣን የሆነ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ለውጥ  ባለበት ዘመን ተቋሙ ራሱን ከለውጥ ጋር የሚያራምድ መሆን እንዳለበትና ለውጡን በፍጥነት ለመረዳትና ለመተንተን  የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ጄኔራል አደም ገልጸዋል። ለውጡ ከአደረጃጀት ጀምሮ የፖለቲካ አስተሳሰብንና ወገንተኝነትን በማስወገድ ገለልተኛ በመሆን መንግስትንና ህዝብን ለማገልገል ያለመ መሆኑን ጠቁመዋል። ተቋሙ  እንደማንኛውም መንግስታዊ ተቋም  ተጠያቂ የሚሆንበት እንዲሁም የስራው ባህሪ እንደተጠበቀ ሆኖ በህግና በህግ በተሰጠው ስልጣን ብቻ የሚሰራ ተቋም መሆን እንዳለበትም ጠቅሰዋል። የአገርንና ህዝብ ደህንነት መጠበቅ የሚቻለው በጥቂት የደህንነት ሙያተኞች ብቻ ባለመሆኑ ከህዝቡ ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ከዚህ በፊት የነበሩ ክፍተቶችን በመለየት እንደሚሰራም ተናግረዋል። ተቋሙ የሚያከናውናቸውን ተግባራት ህዝብ እንዲያውቃቸው የሚያስችል የአሰራር ስርዓት እንደሚዘረጋም ጠቁመዋል። ተቋሙ ከሚፈራ ተቋም ወደ የሚከበር ተቋም በማሸጋገር ህዝቡ ውስጥ በመሆን የህዝብ ደህንነትን ለማረጋገጥ እንደሚሰራ ዳይሬክተር ጄኔራሉ አመልክተዋል። በቀጣይም ብቃት ያለው የሰው ሀይል መፍጠርና ህጋዊ አሰራሮችን ማጠናከር በተቋሙ ትኩረት የሚደረግባቸው ጉዳዮች መሆናቸው ተጠቅሷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም