ፈረንሳይ ሴቶችን ለማብቃት 70 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ እንደምታደርግ አስታወቀች

69

አዲስ አበባ ህዳር 1/2013 (ኢዜአ) የፈረንሳይ መንግሥት ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ሴቶችን ለማብቃት 70 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታወቀ፡፡

የሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች ሚኒስትር ወይዘሮ ፊልሰን አብዱላሂ ከፈረንሳዩ አምባሳደር ሬሚ ማሬሾ ጋር በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል፡፡

ሚኒስትሯ በውይይታቸውም በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ኢትዮጵያ በጾታ እኩልነት፣ ህጻናት መብት፣ ደህንነትና ጥበቃ ዙሪያ ለማከናወን የታቀዱ ተግባራትን ገለጻ አድርገዋል፡፡

አምባሳደር ማሪሾ አገራቸው ኢትዮጵያ  በጾታዊ እኩልነት ዙሪያ ለምታከናውናቸው ተግባራት 70 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ ታደርጋለች ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ እስካሁን የሴቶች፣ ሕጻናት መብት፣ ደህንነትና ጥበቃ ያከናወነቻቸውን ተግባራትን አድንቀዋል፡፡

አገራቸው ተሞክሮዋን ለማካፈል ዝግጁ መሆኗንም አምባሳደር ሬሚ ገልጸዋል፡፡

ሁለቱ አገሮች ዛሬ  የትውልደ ኢትዮጵውያን ጉዲፈቻዎች መረጃ በዘመናዊ ዲጂታል ቴክኖሎጂ የመረጃ ቋት ለመያዝና ጾታዊ እኩልነትን ለማረጋገጥ  በትብብር ለመስራት ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

ኢትዮጵያና ፈረንሳይ ከምዕት ዓመት በላይ የተሻገረ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላቸው አገሮች ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም