ቀጥታ፡

የክልሉን ህዝብ የሠላምና ልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው-- የሲዳማ ክልል ብልጽግና ፓርቲ

ሀዋሳ ኢዜአ ጥቅምት 30/2013 (ኢዜአ) የክልሉን ህዝብ የሠላምና ልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አባላቱንና ደጋፊዎቹን በማስተባበር በትኩረት እየሰራ መሆኑን የሲዳማ ክልል ብልጽግና ፓርቲ አስታወቀ፡፡ 

የፓርቲው አመራሮች የ2013 በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ  ሶስት ወራት የሥራ አፈጻጸም የሚገመግም መድረክ በሀዋሳ ከተማ ተጀምሯል፡፡

በመድረኩ የሲዳማ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አብርሃም ማርሻሎ እንዳሉት ባለፉት ሶስት ወራት ክልሉን የማደራጀት፣ የማቀድና የመፈጸም ተግባራት  በተደራጀ አገባብ በመመራቱ ውጤት አምጥቷል፡፡

ህዝብን ያሳተፈ የአመራር ሥርዓት ለመገንባት በተደረገው ጥረት በልማት ተጠቃሚነትና ተሳታፊነት ከፍ ማድረግ የሚችል አቅም ያለው  አመራር የመፍጠር ሥራ ውጤታማ ነበር ብለዋል፡፡

ፓርቲው እያከናወነ ያለው ተግባር ውጤታማ እንዳይሆን የማደናቀፍ ተልዕኮ ላይ የተሠማሩ አካላትን የመለየት፣ የማንሳትና የመተካት ሥራ መከናወኑን ያመለከቱት አቶ አብርሃም የክልሉን ህዝብ የሠላምና ልማት ተጠቃሚነት  ለማረጋገጥ አባላትና ደጋፊዎችን በማስተባበር በትኩረት እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የህዝቡን የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄ ተረድቶ በተገቢው የሚመልስ አመራር መገንባት ወሳኝ ነው ያሉት ደግሞ በፓርቲው የፖለቲካና ርዕዮተ ዓለም ግንባታ ዘርፍ ሐላፊ አቶ አስፋው ጎነሶ ናቸው፡፡

ለዚህም ፓርቲው የሚመራው የክልሉን መንግስት የልማት ግቦች በጥልቀት አውቆ የሚያገለግሉ አመራሮች ለመፍጠር ክትትልና ድጋፍ እንደሚደርግ ገልጸው የመድረኩ ዓላማ ደካማ አፈጻጸም የታየባቸውን ገምግሞ ማረም መሆኑን አስረድተዋል። 

በመድረኩ የሃዋሳ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ ከክልሉ ሁሉም መዋቅሮች የተወጣጡ ከ350 በላይ የፓርቲው አመራሮች እየተሳተፉ ነው፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም