ኤምባሲዎች ከአካዳሚክ ተቋማት ጋር ተቀራርበው መስራት አለባቸው — በኢትዮጵያ የአዘርባጃን አምባሳደር

3674

አዲስ አበባ ግንቦት 3/2010 የአመራርነት ጥበብ ለአገር ግንባታ ካለው ትልቅ ፋይዳ አንጻር በኢትዮጵያ የሚገኙ ኢምባሲዎች ከአካዳሚክ ተቋማት ጋር ተቀራርበው እንዲሰሩ በኢትዮጵያ የአዛርባጃን አምባሳደር ኢልማን አብዱላይቭ ጠየቁ።

የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የአመራርነትና አስተዳደር ትምህርት ቤት በኢትዮጵያ የአዛርባጃን ኤምባሲ ጋር በመተባበር ‘አመራር ለአገር ግንባታ ቁልፍ ሚና አለው’ በሚል ሃሳብ ሴሚናር አካሄዷል።

በሴሚናሩ በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር ፋቲህ ኡልሶይ ፣ በኢትዮጵያ የአዛርባጃን አምባሳደር ኢልማን አብዱላይቭ ጨምሮ ሌሎች የውጭ አገሮች ዲፕሎማቶች ተሳታፊዎች ነበሩ።

የቀድሞው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ፣ የፖሊቲካ ሳይንስ ምሁሩ ዶክተር መረራ ጉዲናና ሌሎች የከፍተኛ ተቋማት ምሁራንም ተገኝተዋል።

አመራሮች በአገር ግንባታ ያላቸውን ሚና በሚመለከት የኢትዮጵያ፣ አዛርባጃንና ቱርክ ተሞክሮ የቀረበ ሲሆን ፤ የአመራር ጥበብ ጉድለት ጎረቤት ሶማሊያን እንዴት እንዳፈረሳት የሚያሳይ ጥናታዊ ጽሁፍ ከቀረቡት ተሞክሮዎች መካከል አንዱ ነው።

በኢትዮጵያ የአዛርባጃን አምባሳደር ኢልማን አብዱላይቭ ኤምባሲያቸው ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ጋር መስራት ከጀመረ ሁለት ዓመታት እንዳሰቆጠረ አስታውሰው፤ በቀጣይ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በጋራ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

በሴሚናሩ የተገኙ የተለያዩ አገር አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች በኢትዮጵያ ከሚገኙ የአካዳሚክ ተቋማት ጋር  ተቀራርበው እንዲሰሩ ጠይቀዋል።

የአዘርባጃን ኤምባሲ ከዩኒቨርሲቲው ጋር የፈጠረው ትብብር ድልድይ ሆኖ አጋርነቱን በማስተሳሰር ረገድ ያገዘው መሆኑን አምባሳደሩ ጠቁመዋል።

አገራችሁን ለማስተዋወቅ በሴሚናሩ የተገኙ ዲፕሎማቶች ከአካዳሚክ ተቋማት፣ ከዩኒቨርሲቲዎችና ከትምህርት ቤቶች ጋር በጋራ እንዲሰሩ የጠየቁት አምባሳደር ኢልማን ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ጋር የሚሰሯቸውን የትብብር ስራዎች የሚቀጥሉበት መሆኑን ገልጸዋል።

የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ከአዛርባጃን ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጋር ልምድ እንዲለዋወጡ የማድረጉ ስራ መጀመሩንም ተናግረዋል።

አመራሮች በአገር ግንባታ ሂደት ቁልፍ ሚና አላቸው ያሉት አምባሳደሩ፤ አዛርባጃን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በነበረችበት ወቅት አመራሮች በከፈሉት መስዋዕት አገራቸው ዛሬ ላለችበት ደረጃ ማብቃታቸውን ይናገራሉ።

በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የአመራርና አስተዳደር ትምህርት ቤት ዲን ዶክተር አትክልቲ ሃጎስ በበኩላቸው በአገር ግንባታ ሂደት አመራሩ አወንታዊና አሉታዊ ሚና ከአገሮች ተሞክሮ አንጻር ለማየት ሴሚናሩን ማዘጋጀቱን ተናግረዋል።

ከዚህ አንጻር የአገሪቱ በየደረጃው ያሉ አመራሮች የተሰጣቸውን ሃላፊነት በአግባቡ ከተወጡ በአገር ግንባታ ላይ ትልቅ አሻራ እንደሚያኖሩ ገልጸዋል።

ዩኒቨርሰቲው ከተለያዩ የውጭ አገሮች ጋር በቅንጅት በመስራት ጠንካራ አመራር ለመፍጠር እንደሚጥር አክለዋል።