በሠራዊቱ ላይ የተቃጣውን ትንኮሳ እንደሚያወግዙ በደቡብ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ

52

ሐዋሳ ጥቅምት 28/2013 (ኢዜአ) የሀገር ኩራትና ደጀን በሆነው መከላከያ ሠራዊት ላይ ለህዝብና ሀገር ፋይዳ በሌለው ሴረኛ ቡድን የተቃጣው ጥቃት የሚወገዝ ተግባር መሆኑን በደቡብ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ። 

ፓርቲዎቹ ይህን ድርጊት ለመቀልበስ መንግስት የጀመረውን የህግ የበላይነትን የማስከበር ተግባር እንደሚደግፉ ተናግረዋል።

የብልጽግና ፓርቲን ጨምሮ በደቡብ ክልል የሚንቀሳቀሱ ዘጠኝ የፖለቲካ ፓርቲዎች በወቅታዊና ሀገራዊ ሁኔታ ዙሪያ ያላቸውን አቋም የሚገልጽ መግለጫ ሰጥተዋል።

የጌዴኦ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ሊቀ መንበር አቶ አላሣ መንገሻ የፓርቲዎችን አቋም በገለጹበት ወቅት እንዳሉት ባለፉት ሁለት ዓመታት በሃገሪቱ የመጣው ለውጥ ለእውነተኛ የመድበለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታ መሰረት የጣለ ነው።

ባለፉት 27 ዓመታት በነበረው የሴራ ፖለቲካ ምክንያት የተፈጠረውን መጠራጠር በማስወገድ ሃገራዊ አንድነትና ወንድማማችነት ለማምጣት እየተሠራ መሆኑንም ፓርቲዎቹ በጋራ መግለጫቸው ጠቁመዋል።

ሴረኛው የህወሃት ቡድን ለውጡን ለመቀልበስ አፍራሽ ተግባራትን ሲፈጽም እንደነበር ገልጸው መንግስት በሆደ ሰፊነት ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡

ህወሃት ሀገሪቱ እንዳትረጋጋና ለውጡ እንዳይጸና የተለያዩ ሙከራዎችን ቢያደርግም ህዝብ ስላልተቀበለው እየከሸፈ መምጣቱን አስታውቀዋል።

"የለውጥ ሂደቱ ለሁሉም የከፈተውን ሠላማዊ የፖለቲካ ሜዳ በመጠቀም የበደለውን የትግራይን ህዝብ መካስ ሲገባው ለእኩይ ተግባሩ መሸሸጊያ ለማድረግ መሞከሩ ድርጅቱ ለመለወጥ ፍላጎት የሌለው መሆኑን ያሳያል" ብለዋል፡፡

ከሀገራዊ ግዳጁ በተጓዳኝ በልማት ሥራዎች በመሰማራት ህዝቡን ሲያገለግል በነበረው የሰሜን ዕዝ መከላከያ ሠራዊት ላይ የፈጸመው ተግባር በደቡብ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያወግዙት መሆኑንና መንግስት የጀመረውን የህግ የበላይነትን የማስከበር ርምጃ እንደሚደግፉ ገልጸዋል፡፡

በትግራይ ክልል የሚኖረው ማህበረሰብ ከመንግስት ጎን ሆኖ ይህን ሽፍታ ቡድን ለማስወገድ እንዲተባበርም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

መላው ኢትዮጵያውያን ይህ ቡድን በተለያዩ አከባቢዎች ያሰማራቸው የዕኩይ ዓላማው አስፈጻሚዎች ሠላሙን እንዳይነጥቁት በንቃት መጠበቅ እንዳለበት ፓርቲዎቹ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም