የኢትዮጵያና ኤርትራ ወዳጅነት እንዲጎለብት የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሸማግሌዎች ገለጹ

72
ሀዋሳ ሀምሌ 9//2010 በኢትዮጵያና ኤርትራ መንግስታት መካከል ዳግም ያበበው ፍቅርና ወዳጅነት እንዲጎልብት የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሸማግሌዎች ገለጹ፡፡ የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሸማግሌዎቹ ይህንን የገለጹት የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በሀዋሳ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት የኢዜአ ሪፖርተር  በሰጡት አስተያየት ነው፡፡ በዚህ ወቅት የሲዳማ፣ ጌዴኦ፣ አማሮና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አባ ገብርኤል እንዳሉት  በአስመራ ከተማ የኃይማኖቱ መሪ ሆነው ከ1977 ዓ.ም ጀምሮ ለስድስት ዓመታት አገልግለዋል፡፡ በሁለቱ ሀገራት ድንገት በተፈጠረው ግጭት ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸውን ገልፀው  የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች በኃይማኖት፣ በባህልና በሌላም አንድ  መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ " የኤርትራ ህዝብ የተባረከና የተመሰገነ ህዝብ ነው" ያሉት ሊቀ ጳጳሱ ስለኢትዮጵያ ያላቸው የፍቅር ስሜት ከፍ ያለ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡ በሁለቱ ሀገራት መካከል አሁን የተፈጠረው  ሰላምና እንደገና ያበበው ፍቅር ተጠናክሮ  እንዲጎልበት ከመንግስት ጎን  በመቆም የድርሻቸውን እንደሚወጡን ገልጸዋል፡፡ ለዘመናት ተነፋፍቀው የቆዩት የኤርትራና ኢትዮጵያ ህዝቦች የተገናኙበት ታሪካዊ ክስተት በመሆኑ ለሁለቱ አሀራት ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካና ለሰላም ወዳድ ዓለም ህዝብም የደስታ ቀን መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የደቡብ ህዝቦች ክልል የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አብዱልከርም ሼህ ሁሴን ናቸው፡፡ " እርቀ ስላሙ ለአብሮነት፣ ለሰላማችንና ለእድገታችን ትልቅ አስተዋፅኦ ያለው ቀና ድርጊት በመሆኑ አንድነታችንን የማስቀጠል ኃላፊነት ለመንግስት ብቻ ሳንተው የኀይማኖት አባቶችም በየእምነት ተቋማት ለትውልድ የሚቀር ታሪካዊ ስራ በጋራ እንሰራልን "ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ ወንገላዊት ቤተክርስትያን የሲዳማና ሃዋሳ ከተማ ሰበካ ቅርንጫፍ ኃላፊ ቄስ ሞላ በርዳሞ እንደገለጹት ቋንቋው ይለያይ እንጂ የሰው ዘር በሙሉ አንድ ነው፡፡ "የኃማይኖት አባቶችም ይህ አንድነት ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ሰው ሁሉ በፍቅር እንዲኖር ይቅርታ የማድረግ ባህል እንዲለመድ በኃላፊነት መስራት አለብን"  ነው ያሉት ቄስ ሞላ፡፡ የሀገር ሸማግሌው  አቶ አለሙ አዳሙ  በበኩላቸው ከጊዜ በኋላ በተፈጠረው ግጭት ተለያይተው ይቆዩ እንጂ ኢትዮጵያዊያን እና ኤርትራዊያን  አንድ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ባህላቸውና ኃይማኖታቸው ተመሳሳይ በመሆኑ በአንድነት ተባብረው የሚኖሩ ሰዎች እንደነበሩና አሁን በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ አብሮነታቸው ተጠናክሮ እንዲቀጠል ፍላጎታቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ሰላም መውረድ ታላቅ ደስታ እንደፈጠረባቸው የተናገሩት ደግሞ ሌላው የሀዋሳ ከተማ የሀገር ሽማግሌ አቶ አብነው ማሰቦ ናቸው፡፡ ግጭት ለማንም ጥቅም ስለሌለው ከኃይማት አባቶችና ከመንግስት ጋር በመሆን የተጀመረውን የሰላም እንዲጎልበት ለመደገፍ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የሁለቱ ሀገራት መንግሰታት ፍቅር ይሻለናል ብለው እርቀ ሰላም እንዲውርድ  ማድረጋቸው ተባብሮ ለመስራትና የጋራ ተጠቃሚ ለመሆን  ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው  የሀገር ሽማግሌዎቹ አስረድተዋል፡፡ የሁለቱ ሀገራት ፍቅርና ወዳጅነት እንዲጎልበት የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸው ሁለቱ መንግስታት ሰላም፣ ፍቅርና ወዳጅነት እንዲወርድ ላደረጉት ጥረት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም