ምክር ቤቱ በትግራይ ክልል ለ6 ወር የሚጸና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን አጸደቀ

አዲስ አበባ ጥውምት 26/2013 9 (ኢዜአ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በትግራይ ክልል ላይ ለስድስት ወር የሚጸና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን በሙሉ ድምጽ አጸደቀ።

ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 6ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ስብሰባው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ህገ-መንግስቱንና ህገ-መንግስታዊ ስርአቱን ከአደጋ ለመከላከል ትናንት ያወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርምሮ አጽድቋል።

በትግራይ ክልል የአገር ሉአላዊነትን የሚገዳደሩ ህገ ወጥ ተግባራትን እየተፈጸሙ በመሆኑ አዋጁ ማስፈለጉ ተገልጿል።

እየተፈጸሙ ያሉ ህገ ወጥ ተግባራትን በመደበኛ የህግ ማስከበር ስርአት ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከማይቻልበት ደረጃ በመድረሱም አዋጁ አስፈልጓል።

አዋጁ ህግና ስርአትን ለማስከበር አስፈላጊ ስለመሆኑም የምክር ቤቱ አባላት አንስተዋል።

የምክር ቤቱ አባላት በአዋጁ አስፈላጊነት ላይ ከተወያዩ በኋላ በሙሉ ድምጽ አጽድቀውታል።

በተመሳሳይ ሰባት አባላት ያሉት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ አባላትን ለመሰየም በቀረበለት የውሳኔ ሃሳብ ላይም ምክር ቤቱ ተወያይቷል።

የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ ከተወያየ በኋላ በ6 ተቃውሞ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል።

አዋጁ ለስድስት ወራት የሚጸና ሲሆን እንደ አስፈላጊነቱ ለተጨማሪ 4 ወራት እንደሚራዘም ተገልጿል።

የኢፌዴሪ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ትናንት ባካሄደው 21ኛ አስቸኳይ ልዩ ስብሰባ በትግራይ ክልል ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም