የትግራይን ህዝብ ሰላም በሚጠብቀው የመከላከያ ሰራዊት ላይ የተፈጸመው ጥቃት አሳፋሪ ነው- አቶ ኡሞድ ኡጁሉ

78

ጋምቤላ፣  ጥቅምት 25/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያን ለመበታተን ሲንቀሳቀስ የቆየው ህወሃት የትግራይን ህዝብ ደህንነት ሲጠብቅ በኖረው የሃገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመው ጥቃት አሳፋሪ ድርጊት ነው ሲሉ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ-መስተዳደር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳደሩ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት ላለፉት 20 ዓመታት የትግራይ ህዝብን ሰላምና ደህንነት ሲጠብቅ በቆየው የሃገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ህወሃት የፈጸመው ድርጊት የሃገር አፍራሽነቱን ያሳየ ነው።

"በጥቂት ሃገር አፍራሽ የህወሃት ቡድን ምክንያት ወገናችን የሆነው የትግራይ ህዝብ በድጋሚ ለችግር እንዳይጋለጥ የፌዴራል መንግስት ጉዳዮችን በሰከነ አካሔድ በትዕግስት ማሳለፉን መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በሚገባ ያውቃል"ብለዋል።

የህወሃት አጥፊ ቡድን ያሰማራው የክልሉ ልዩ ኃይል ጥቃት መፈጸሙ ኢትዮጵያን ከአፍሪካ ቀንድ ለማጥፋት ቡድኑ ሲሰራ እንደነበረ በገሃድ ያሳየ ተግባር መሆኑንም ርዕሰ መስተዳደሩ አስታውቀዋል።

"ቡድኑ እንደፈለገ ሲፎክር ምንም ዓይነት ጣልቃ ሳይገባ በገለልተኝነት የሃገርና የህዝብን ሉአላዊነትን እየጠበቀ ባለው በራሱ ሃገር ጦር ላይ ጦርነት መክፈትን ያክል የሃገር ክህደትና አሳፋሪ ድርጊት የለም" ብለዋል በመግለጫቸው።

ሃገር የማፈራረስና የኢትዮጵያን ህዝብ ብሄራዊ ጥቅምና ሉአላዊነት ለባዕድ አሳልፎ የመስጠት አጀንዳ ይዞ የሚንቀሳቀሰውን የህወሃት አጥፊ ቡድን ድርጊት የጋምቤላ ክልል ህዝብና መንግስት በጽኑ የሚያወግዘው መሆኑንም አስረድተዋል።

"የቡድኑን እንቅስቃሴ በመቀልበስ ሃገራችን የጀመረችውን የብልጽግና ጉዞ ለማስቀጠል በሚደረገው ጥረትም የጋምቤላ ክልል ህዝብና መንግስት ከፌዴራል መንግስትና ከመከላከያ ሰራዊታችን ጎን እንደሚቆም አረጋግጣለሁ"ብለዋል።

በአፍራሽ ቡድኑ ጥቃት ማዘናቸውን የገለጹት ርዕሰ-መስተዳደሩ ችግሩን ለመቀልበስ በሚደረገው ማንኛውም እንቅስቃሴ ላይ የክልሉ ህዝብ የነቃ ተሳትፎ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም