በምሥራቅ ወለጋ ባለፉት ሶሰት ወራት ከ149 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ - ኢዜአ አማርኛ
በምሥራቅ ወለጋ ባለፉት ሶሰት ወራት ከ149 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ
ነቀምቴ፣ ጥቅምት 21/2013 (ኢዜአ) በምሥራቅ ወለጋ ዞን በተያዘው የበጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ሶሰት ወራት ከተለያዩ የገቢ ምንጮች 149 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን የዞኑ የገቢዎች ባለሥልጣን ገለጸ።
የባለሥልጣኑ ሥራ አስኪያጅ አቶ መኮንን ዲቢሣ እንዳሉት ገቢው የተገኘው ከማዘጋጃ ቤት አገልግሎት፣ ከንግድ ዘርፍና ከሌሎችም ምንጮች ነው።
ፈጻጸሙ ከእቅዱ 40 ሚሊዮን ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ደግሞ በ117 ሚሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው ገልጸዋል።
በየደረጃው ያለው አመራርና የባለ ሥልጣኑ ሠራተኞች ከግብር ከፋዩ ህብረተሰብ ጋር በቅርበት ተገናኝተው በመወያየት የመንግሥት ግብር በወቅቱ እንዲሰበሰብ ባደረጉት ጥረት ብልጫ ያለው ገቢ እንዲኖር ማስቻሉን ሥራ አስኪያጁ አስረድተዋል።
ከንግዱ ማህበረሰብ መካከል በጉቶ ጊዳ ወረዳ የኡኬ ቀበሌ ነዋሪ እና በሆቴል ሥራ ላይ የተሰማሩት ወይዘሮ ብዙነሽ ደምሴ በሰጡት አስተያየት ግብር መክፈል የዜግነት ግዴታ መሆኑን በመረዳት የሚፈለግባቸውን ግብር በወቅቱ መፈጸማቸውን ተናግረዋል፡፡
የዚሁ ቀበሌ ነዋሪና በእርሻ ሥራ ላይ የተሰማሩት አቶ ተጫኔ ደባልቄ በበኩላቸው የሚጠበቅባቸውን 3 ሺህ 957 ብር ግብር በወቅቱ መክፈላቸውን ገልጸዋል።
በዋማ አገሎ ወረዳ በሁሉን አቀፍ የገጠር መንገድ ተደራሽ ሥራ ላይ የተሰማሩ የኢ.ኤም.ኬኬ.ኤም ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ምትኩ ጌታቸው ከድርጅቱ የሚፈለገውን አንድ ሚሊዮን 600 ሺህ ብር የመንግሥት ግብር በወቅቱ በመክፈል የዋንጫ ተሸላሚ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
በምሥራቅ ወለጋ ዞን በተያዘው የበጀት ዓመት ከ476 ሚሊዮን 600 ሺህ ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱም ተመልክቷል።