ወደ ዩኒቨርሲቲ ለሚገቡ ተመራቂ ተማሪዎች በቂ ትራንስፖርት ተዘጋጅቷል- የትራንስፖርት ባለስልጣን

58

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21/2013 ( ኢዜአ) ወደ ዩኒቨርሲቲ ለሚገቡ ተመራቂ ተማሪዎች በቂ የትራንስፖርት አገልግሎት መዘጋጀቱን የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ገለጸ።


ከጥቅምት 23 እስከ 30 ቀን 2013 ዓ.ም ባሉት ቀናት ተመራቂ ተማሪዎችን እንዲቀበሉ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር መመሪያ አስተላልፏል።

በዚሁ መሰረት ዩኒቨርሲቲዎች ለተመራቂ ተማሪዎች ጥሪ ማድረጋቸውን ተከትሎ የትራንስፖርት ችግር እንዳይገጥም የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን በቂ ዝግጅት ማድረጉ ታውቋል።

በባለስልጣኑ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ብቃት ማረጋገጫ ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ በላቸው ለኢዜአ እንደገለጹት ተማሪዎቹ የጉዞ ችግር እንዳይገጥማቸው በቂ አውቶቡስ ተዘጋጅቷል።

የትራንስፖርት አገልግሎቱ ተማሪዎች እንዳይጉላሉ ሲባል ከመናኸሪያ እስከሚማሩበት ዩኒቨርሲቲ ድረስ የማጓጓዝ አገልግሎት ትብብርን መሰረት ባደረገ መልኩ እንደሚሆንም ጠቁመዋል።

የተማሪዎቹን የትራንስፖርት አገልግሎት ከፀጥታ ተቋማት ጋር በቅንጅት ለመስራት ዝግጅት መደረጉንም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

በባለስልጣኑ የአዲስ ከተማ ሀገር አቋራጭ መናኸሪያ የስምሪትና ቁጥጥር ባለሙያ አቶ አረጋ አዲስ ተማሪዎች በጉዞ ወቅት እንዳይጉላሉ ከፖሊስ፣ ከትራንስፖርት ማህበራት እንዲሁም ከጫኝና አውራጆች ጋር በጋራ መስራት የሚያስችል ዝግጅት አድርገናል ብለዋል።

የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ሲባል በጉዞ ወቅት ተማሪዎች አስገዳጅ የጤና መመሪያዎችን ሊተገብሩ ይገባልም ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም