ከተሞች ሁለንተናዊ ችግሮችን በጋራ ሊፈቱ እንደሚገባ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር አሳሰበ

172

አዲስ አበባ ጥቅምት 20/2013 (ኢዜአ) ከተሞች እርስ በርስ በመደጋገፍ የሚገጥሟቸውን ሁለንተናዊ ችግሮች በጋራ መፍታት እንደሚገባቸው የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር አሳሰበ።

የኢትዮጵያ ከንቲባዎች ፎረም ዛሬ ተመስርቷል።

“የተሻለ ከተማ ለተሻለ ህይወት” በሚል መሪ ሀሳብ በአገር አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያ ከንቲባዎች ፎረም የመመስረቻ ስነ ስርዓት ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ  ተካሂዷል።

የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሃመድ በፎረሙ ምስረታ ላይ እንዳሉት፤ ከተሞች የነዋሪዎቻቸውን ወቅታዊና መጻኢ ዘመን የተሻለ ለማድረግ ከምንጊዜውም በላይ በጋራ መስራት ይጠበቅባቸዋል።

ለዚህ ደግሞ ያላቸውን መልካም ዕድል፣ ፀጋ እና ተግዳሮት በወቅቱ የሚረዳና የእርስ በእርስ ግንኙነቶችን የሚያጠናክር መሪ  እንደሚያስፈልጋቸው ነው የገለጹት።

ከተሞች የፈጠራና የልሕቀት ማዕከል፣ የሕብረ ብሔራዊ ሁነት መገለጫና የብለጽግና መሰላል መሆናቸውን አመልክተው፤ "በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የበርካታ እሴት ባለቤት የሆኑ ሕዝቦች በሚኖሩባቸው ከተሞች ከንቲባዎች በመቀራረብ ልምዳቸውን ሊለዋወጡ ይገባል" ብለዋል።

ከተሞች ከግጭት ርቀው የአብሮ መኖር ማሳያ እንዲሆኑ ከንቲባዎች ጉልህ ሚና መጫወት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

በአሁኑ ወቅት ከተሞችን ሰላማዊና ለነዋሪዎቻቸው የሚመቹ ከማድረግ በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር እንደሌለ አመልክተው፤ በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባም ገልጸዋል።

የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር መስፍን አሰፋ በበኩላቸው፤ ከተሞች ከእለት ወደ እለት እያደገ የመጣውን የከተማ ነዋሪ ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎት ለማሟላት በጋራ መስራት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የከተማ ነዋሪዎች ቁጥር 22 በመቶ መሆኑንና በየዓመቱም ከ4 ነጥብ 2 በመቶ በላይ እድገት እያሳየ መሆኑን ጠቁመው፣ "ፎረሙ መመስረቱ በተደራጀ መንገድ ለመንቀሳቀስና ይህንን ኃይል በተገቢው መንገድ ለማስተዳደር ያስችላል" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ከንቲባዎች ፎረም እያንዳንዱ የከተማ ከንቲባ የተሻለ ልምዱን የሚያጋራበት፣ ለሚገጥሙ ችግሮች በጋራ መፍትሔ የሚያፈላልጉበት እና የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ዕውቅና የሚሰጥበት መሆኑ ተገልጿል።

ፎረሙ ተግባር ተኮር የሆኑና ችግር ፈቺ መፍትሔዎችን ማስፋፋት እና ሌሎችም እንዲጠቀሙበት ማስቻልን ዓላማ አድርጎ ይሰራልም ተብሏል።

የፎረሙ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ፎረሙ መመስረቱ አንዱ ከሌላው ልምዱን ለመለዋወጥና ለመደጋገፍ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

ሕዝብን በተቀናጀ መንገድ ለማገልገልና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እንደሚረዳም አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም