የልጆችን የንባብ ተሳትፎ የሚያነቃቃ መርሃግብር ይፋ ሆነ

46

አዲስ አበባ ጥቅምት 20/2013 (ኢዜአ) ኮሮናቫይረስ መከሰቱን ተከትሎ የትምህርት ተቋማት በመዘጋታቸው የተዳከመውን የልጆች የንባብ ተሳትፎ ለማነቃቃት የሚረዳ የንባብ መርሃግብር ይፋ ሆነ። 

የንባብ መርሃግብሩ ዛሬ ይፋ የተደረገው በጎተራ የጋራ መኖሪያ ሕንጻ የነዋሪዎች ማህበር ቤተ መጻህፍት ነው።

መርሃግብሩን ይፋ ለማድረገ በተዘጋጀው መርሃግብር ላይ ንግግር ያደረጉት የቄርቆስ ክፍለ ከተማ  ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል ረዲ "ከልማት ሁሉ የላቀው ልማት የህጻናትን አዕምሮ ማልማት ነው" ብለዋል።

ኮሮናቫይረስ በኢትዮጵያ ውስጥ መከሰቱን ተከትሎ ትምህርት ቤቶች በመዘጋጀታቸው በርካታ ህጻናት በቤት ውስጥ ለመዋል መገደዳቸውንና የንባብ ተነሳሽነታቸው መዳከሙን ተናግረዋል።       

"ከጊዜ ወደጊዜ እየተዳከመ ያለውን የልጆችና የአዋቂዎች የንባብ ባህልን ማጠናከር ያስፈልጋል" ብለዋል ።

 ከልማቶች ሁሉ የላቀው ልማት የታዳጊ ህጻናት አዕምሮ ማልማት መሆኑን ገልጸው ለእዚህ ቅድሚያ መስጠት እንደሚገባ አቶ ጀማል አመልክተዋል።

በዚህም ልጆች አልባሌ ቦታዎች እንዳይውሉ ከማድረግ ባለፈ ልጆች ማንነታቸውን በአግባቡ ለመቅረጽና ነገ አገርን መገንባት የሚችሉ ትውልዶችን ለማፍራት እንደሚቻል አመልክተዋል።

የንባብ ባህል በተሻለ እየተጠናከረ እንዲመጣ የአትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻህፍት ኤጀንሲና የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ እገዛ እንዲያደርጉም አቶ ጀማል ጥሪ አቅርበዋል።

የአትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻህፍት ኤጀንሲ ዋና  ዳይሬክተር አቶ ይኩኑአምላክ መዝግቡ በበኩላቸው የህጻናትን የንባብ ባህል ለማሳደግ የሚሰሩ ሥራዎች ለራስም ሆነ ለአገር ትልቅ አስተዋዖ የሚያበረክቱ መሆናቸውን ተናግረዋል።

"በቀጣይም አዲስ አበባ የንባብ ከተማ እንድትሆን ለማድረግ ሁሉም የድርሻውን መወጣት ይኖርበታል" ብለዋል።

የልጆችን የንባብ ተሳትፎ ለማሳደግ ዛሬ በጎተራ የጋራ መኖሪያ ሕንጻ የነዋሪዎች ማህበር ቤተ መጻህፍት ይፋ የሆነው መርሃ ግብር በቃጣይ በ5 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለ10 ሳምንታት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ታውቋል።

ዛሬ ይፋ የሆነው የንባብ መርሃግብር የአትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻህፍት ኤጀንሲ ከኢጋ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ሲሆን በመርሃግብሩ ላይ የመጻህፍት አወደ - ርዕይና ሽያጭም ተከናውኗል።

በመርሃግብሩ ይፋ የቄርቆስ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጸሚ፣ የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻህፍት ዋና ዳሬክተርና የተለያዩ የወረዳና የክፍለ ከተማ አመራሮች፣ ወላጆችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም