የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበርና ዲ.ኤስ.ቲቪ በሚቀጥለው ሳምንት የውል ስምምነት ይፈፅማሉ

77

አዲስ አበባ ጥቅምት 20/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበርና የደቡብ አፍሪካ ዲጂታል ሳተላይት ቴሌቪዥን (ዲኤስቲቪ) የፕሪሚየር ሊግ ውድድር የቀጥታ ቴሌቭዥን ስርጭትና የውድድር ስያሜ ውል ስምምነት በሚቀጥለው ሳምንት እንደሚፈራረሙ ተገለጸ።

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ኩባንያ የፕሪሚየር ሊግ ውድድሩን በቀጥታ ቴሌቪዥን ስርጭት ለማስተላለፍ ፍላጎት ያላቸውን ድርጅቶች ባወጣው ጨረታ መሠረት ሲያወዳድር ቆይቷል።

የደቡብ አፍሪካ ዲጂታል ሳተላይት ቴሌቪዥን (ዲኤስቲቪ) ጨረታውን በማሸነፍ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር የቀጥታ ቴሌቭዥን ስርጭትና የውድድር ስያሜን በመስከረም ወር 2013 ዓ.ም በ22 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር መግዛቱ የሚታወስ ነው።

ዲኤስቲቪ የፈረንሳዩ የቴሌቪዥን ድርጅት ካናል ፕላስን ጨምሮ ሌሎች ዓለም አቀፍ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን አሸንፎ ነው የስያሜ መብቱን የገዛው።

ጨረታውን ያሸነፈውም ዲኤስቲቪ ያቀረበው የቴክኒክና የፋይናንስ ትልመ ሀሳብ (ፕሮፖዛል) የተሻለ ሆኖ በመገኘቱ እንደሆነ በወቅቱ ተገልጾ ነበር።

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሰይፈ የቀጥታ ቴሌቭዥን ስርጭትና የውድድር ስያሜ ውሉ ስምምነት በሚቀጥለው ሳምንት እንደሚፈረም ለኢዜአ ገልጸዋል።

ዛሬ ከዲኤስቲቪ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በተደረገ ውይይት ውሉ በቀጣዩ ሳምንት እንደሚፈረም መግለጻቸውንም አመልክተዋል።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግን የሚያስተላልፈው ዲኤስቲቪ በጨዋታ ስርጭት ቅድመ ዝግጅት ዙሪያ ለመነጋጋር ከደቡብ አፍሪካ ሦስት አባላት ያሉት ቡድን ማምሻውን አዲስ አበባ መግባቱን አቶ ክፍሌ ጠቁመዋል።

የመጡት ሰዎች የዲኤስቲቪ የኢትዮጵያ ተወካይ፣ የዲኤስቲቪ የስርጭት (ፕሮዳክሽን) ኃላፊና የስርጭት ባለሙያ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የልዑካን ቡድኑ አባላትም የጨዋታ ስርጭትን አስመልክቶ ባሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት እንደሚያደርጉና የስታዲየሞችን ዝግጁነት እንደሚመለከቱም ገልጸዋል።

"የጨዋታ መርሃ ግብሮች፣ ውድድር የሚካሄድባቸው ስታዲየሞች፣ የፕሪሚየር ሊጉ ውድድር ዕጣ አወጣጥ፣ ከጨዋታ በፊት በጨዋታ ጊዜና ከጨዋታ በኋላ መሟላት ባለባቸው ሁኔታዎች እንዲሁም በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ውይይት ይደረጋል" ብለዋል።

አቶ ክፍሌ ከልዑካን ቡድኑ ጋር የመጀመሪያው ውይይት ዛሬ ከእኩለ ቀን በፊት መደረጉንም ተናግረዋል።

የስታዲየሞች ዝግጁነት በተመለከተ የልዑካን ቡድኑ ነገ አዲስ አበባ ስታዲየምን፣ ከነገ በስቲያ የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየምን እንደሚመለከት ገልጸዋል።

የልዑካን ቡድኑ ውይይቱንና ምልከታውን አጠናቆ ሰኞ ጥቅምት 23 ቀን 2013 ዓ.ም ወደ ደቡብ አፍሪካ እንደሚመለስም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ታህሳስ 3 ቀን 2013 ዓ.ም እንደሚጀመር መገለጹን ያስታወሱት አቶ ክፍሌ፣ በሊጉ የመጀመሪያ 23 ቀናት የሚደረጉ ጨዋታዎች በአዲስ አበባ ስታዲየም እንደሚካሄዱ ገልጸዋል።

የፕሪሚየር ሊጉ ጨዋታዎች የሚካሄዱባቸውን ስታዲየሞች አስመልክቶ በቀጣዩ ሳምንት ዝርዝር መረጃዎች ይፋ እንደሚሆኑም ነው የገለጹት።

የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦችና ተጫዋቾች ውድድሩን ለማካሄድ በወጣው የኮቪድ-19 መመሪያ አማካኝነት አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ዝግጅት እያደረጉ እንዲቆዩ ሥራ አስኪያጁ ጥሪ አቅርበዋል።

የደቡብ አፍሪካው ኩባንያ መልቲቾይዝ እ.አ.አ በ1995 የተቋቋመ ሲሆን ዲኤስቲቪን ጨምሮ ሌሎች የሳተላይት ቴሌቪዥንና የበይነ መረብ የተንቀሳቃሽ ምስል አማራጮችን በስሩ የያዘ ነው።

ትኩረቱን ከሰሀራ በታች በሚገኙ አገራት ያደረገው ኩባንያው በ50 የአፍሪካ አገራት 14 ሚሊዮን የሚጠጉ ደንበኞች እንዳሉት መረጃዎች ያሳያሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም