የአእምሯዊ ንብረት ጥበቃ ስራዎችን ለክልሎች ለማዳረስ በትኩረት እንደሚሰራ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የአእምሯዊ ንብረት ጥበቃ ስራዎችን ለክልሎች ለማዳረስ በትኩረት እንደሚሰራ ተገለጸ

አዳማ ጥቅምት 20/2013 (ኢዜአ) የአእምሯዊ ንብረት የጥበቃ ስርዓትና የልማት ስራዎችን ለክልሎች ለማዳረስ በትኩረት እንደሚሰራ የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት ገለጸ።
ጽሕፈት ቤቱ ከክልሎች ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኤጄንሲዎችና ቢሮዎች ጋር በቀጣዩ አስር ዓመት የአእምሯዊ ንብረት ልማትና ጥበቃ እቅድ ዙሪያ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተወያይቷል።
የጽሕፈት ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ እንዳሉ ሞሲሳ እንደገለጹት ውይይቱ የአእምሯዊ ንብረት የጥበቃ ስርዓትና የልማት ስራዎችን ለክልሎች ለማዳረስ ከሚመለከታቸው ሴክተሮች ጋር በእቅዱ ዙሪያ ግልፅ ግንዛቤና እውቀት እንዲኖረ ለማስቻል ነው።
ለተፈፃሚነቱ በቅንጅት ለመስራት እንደሆነ አመልክተዋል።
አገልግሎቱን በተቀናጀ መልኩ ለተገልጋዮች ለማድረስም እቅዱን በአግባቡ መገንዘብ ይኖርበናል ብለዋል።
በተለይም የቴክኖሎጂ፣ የባህላዊ እውቀት ፈጠራዎች፣ የግብርና ውጤቶችና የቅጂ መብቶች ጥበቃ እንዲያገኙና እንዲለሙ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ጋር በቅንጅት ለመስራት በእቅዱ ትኩረት መደረጉን ገልጸዋል።
በመሪ እቅዱ ሀገር በቀል እውቀቶች በተለይም የግብርና ምርቶች፣ የባህል ህክምና፣የዕደ ጥበብ ዕውቀቶች በሀገር አቀፍ ደረጃ ጥበቃ እንዲደረግላቸው ስርዓት የመፍጠር ስራ እንደሚከናወንም ተናግረዋል።
ለዚህም የህግ ማእቀፎችና አሰራሮችን የማሻሻል እንዲሁም የተፈጻሚነት ደረጃቸውን የማስፋትና የማሳደግ ተግባራት በተቀናጀ መልኩ ተፈጻሚ እንደሚሆንም አስረድተዋል።
ቀደም ባለው ዘመን ከ29 ሺህ በላይ የቴክኖሎጂ፣ የፈጠራ ባለቤትነት መብትና የቅጂ መብቶችን ማመልከቻ ጽሕፈት ቤቱ ተቀብሎ ጥበቃ እንዲደረግላቸው ማድረጉን የገለጹት ደግሞ በጽሕፈት ቤቱ የእቅድ ክትትልና ግምገማ ዳይሬክተር አቶ ወንድወስን ግዛቸው ናቸው።
ጥበቃ እንዲያገኙ ከተደረጉት ውስጥ 21ሺህ የንግድ ምልክቶች እና 6ሺህ 934 የፈጠራ ባለቤትነት (ፓተንት) ይገኙበታል።
በሚቀጥሉት አስር ዓመታትም የቴክኖሎጂ መረጃዎችን ማሰራጨት ብቻ ግብ ባለመሆኑ የፈጠራ ውጤቶች ተሻሽለው ህብረተሰቡ ዘንድ ለማድረስ ጭምር በእቅዱ ትኩረት ማድረጋቸውን አመልክተዋል።