የኢትዮጵያኛ ኤርትራ ግንኙነት የሁለቱን ሃገራት ህዝቦች ወዳጅነት ዳግም ያጠናክራል...የደባርቅ ከተማ ነዋሪዎች

98
ደባርቅ ሐምሌ 9/2010 ኢትዮጵያና ኤርትራ የጀመሩት አዲስ የግንኙነት ምእራፍ የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች የቆየ ወዳጅነት ዳግም የሚያጠናክር በመሆኑ ከልብ እንደግፈዋለን ሲሉ የደባርቅ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ። ነዋሪዎቹ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን የለውጥ እርምጃ ለማሳካት መዘጋጀታቸውን ዛሬ ባደረጉት የድጋፍ ሰልፍ አስታውቀዋል። የሰልፉ ተሳታፊ አቶ በላይ መኮንን "ለድጋፍ ሰልፉ የወጣሁት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ሰላምን በማምጣት ለአንድነትና ለፍቅር ሁላችንንም ለማስተሳሰር የፈጸመው ተግባር ከልቤ ውስጥ ዘልቆ በመግባት ትልቅ ደስታ በመፍጠሩ ነው" ብለዋል። "ኢትዮጵያና ኤርትራ ወትሮም በባህል በቋንቋና አብሮ በመኖር የተሳሰሩ ህዝቦች ነበሩ" ያሉት አቶ በላይ ላለፉት 20 ዓመታት ተቋርጦ የነበረው ግንኙነት ዳግም ተመስርቶ ሁለቱ መሪዎች መገናኘታቸው እንዳስደሰታቸውም ተናግረዋል። "የተጀመረው ለውጥ እንዲቀጥል የኢትዮጵያ ህዝብ አንድ ሆኖ ትግሉን በጨዋነት ይዞ መጓዝ አለበት" ያሉት ደግሞ ሌላው ተሳታፊ አቶ መኳንንት ደሳለኝ ናቸው። "ዶክተር አብይ አህመድ በማይታመንና ባልጠበቅነው ሁኔታ አስመራ ገብቶ የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች ግንኙነት እንዲቀጥል ማድረጉ አስደሳች ነው" ብለዋል፡፡ ሌላው ተሳታፊ ወጣት ብርሃን አስማማው በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተጀመረው ሀገራዊ የለውጥ እርምጃ ከዳር እንዲደርስ አጋርነቱንና ከጎናቸው መሆኑን ለማረጋገጥ በሰልፉ መካፈሉን ተናግሯል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአሁኑ ሰዓት በሃገሪቱና በአካባቢው ሃገሮች ዘንድ ሰላማዊ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዲፈጠር የሚያደርጉትን ጥረት እንደሚያደንቅም ገልጿል። "ዶክተር አብይ አህመድ ለእኔ ነብዩ ሙሴ ወይም ነብዩ ኤርሚያስ ነው" ያለው ወጣት ሀገርአለም ሲሳይ ደግሞ “ከወንድሞቻችን ኤርትራውያን ጋር እንድንገናኝ ታላቅ ተግባር ያከናወነ መሪ ነው” ብሏል። በቀጣይም የጠቅላይ ሚኒስትሩን አመራር በመከተል ለውጡን ለማገዝ የሚጠበቅበትን ሁሉ እንደሚያከናውን ተናግሯል። የድጋፍ ሰልፉ ዋና አስተባባሪ አቶ መላኩ በሪሁን እንደገለጹት የሰልፉ አላማ እየመጣ ያለውን ለውጥ ለመደገፍና ለለውጡ ተዋናይ ዶክተር አብይ አህመድና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች እውቅናና ድጋፍ ለመስጠት ነው። ይህ ለውጥ እንዲመጣ ከሌሎች ብሄር ብሔረሰቦች ጋር በመሆን አማራ ክልል ሕዝብ በግንባር ቀደምትነት ትግል ማድረጉንም አስረድተዋል። የደባርቅ ከተማ ከንቲባ አቶ ሀይለጊዮርጊስ ሙሉጌታ "የጥላቻ ግድግዳ ፈርሶ ኢትዮጵያና ኤርትራ በፍቅር አብሮ ለመኖር ቃል በገቡበት ማግስት የደባርቅ ከተማ ህዝብ ለድጋፍ መውጣቱ ታሪካዊ ያደርገዋል" ብለዋል። እየታየ ያለውን የለውጥ ሒደት ለመደገፍ ትናንት በተደረገው ሰልፍ ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች በመውጣት ተሳታፊ ሆነዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም