በአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛና ቴክኒክ ብቃት ምርመራ ተቋማት ያሉ ችግሮች ለትራንስፖርት ዘርፍ ማነቆ እንደሆኑ ተገለጸ

82

አዳማ ጥቅምት 18/2013 (ኢዜአ) በአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛና ቴክኒክ ብቃት ምርመራ ተቋማት ያሉ ችግሮች ለትራንስፖርት ዘርፍ አገልግሎት አሰጣጥ ማነቆ መሆናቸውን የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ገለጸ።

ባለስልጣኑ ከአሽከርካሪዎች ማስልጠኛ፣ ቴክኒክ ብቃት ምርመራ ተቋማትና ባለድርሻ አካላት  ጋር በዘርፍ በተካሄደው የጥናት ግኝት ላይ ዛሬ በአዳማ መክሯል።

የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር  አቶ ምትኩ አስማረ እንደገለጹት  ማሰልጠኛ ተቋማቱ የተሟላ የማሰልጠኛ ግብዓት ሳይኖራቸው በአሮጌና ከመስመር ወጪ በሆኑ ተሽከርካሪዎች ስልጠና እየሰጡ ነው።

በዚህም ሰልጣኞቹ ተገቢውን ዕወቀትና ክህሎት ሳያገኙና ለሙያው ብቁ ሳይሆኑ ወደ ስራ በመግባት ለሰው ህይወትና ንብረት መጥፋት  መንስኤ እየሆኑ መምጣታቸውን  አስረድተዋል።

በዚህም ምክንያት ለትራንስፖርት አግልግሎት አሰጣጥ ማነቆ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ችግሩን ለማቃለል  በትራንስፖት ሚኒስቴር አስተባባሪነት   በአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛና የፍቃድ አገልግሎት፣ የተሽከርካሪ የቴክኒክ ምርመራና ብቃት ማረጋገጥ ላይ ጥናት መድረጉን አስታውቀዋል።

የምክክር መድረኩ ዓላማ ከጉዳዩ ባለቤቶችና ባለድርሻ አካል ጋር በጥናቱ ግኝትና የመፍትሔ አቅጣጫ ላይ በመወያየት  በክልሎችና ፌዴራል ደረጃ ወጥ የሆነ የስልጠናና አሰራር ስርዓት እንዲኖ ነው ብለዋል።

በመድረኩ ጥናቱን ያቀረቡት በትራንስፖርት ሚኒስቴር የቴክኒክ አማካሪ አቶ ታምሩ ፉፋ  ጥናቱ ሰፊ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ የሚታይባቸው 20 ዞኖችና አዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ 129 የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛና የቴክኒክ ብቃት ማረጋገጫ ተቋማት መካሄዱን ገልጸዋል።

በሀገሪቱ  ከሚንቀሳቀሱት ተሽከርካሪዎች ውስጥ 40 በመቶ የሚሆኑት ያረጁና ከ10 ዓመት በላይ ያገለገሉ ፣  78 በመቶ የሚሆነው የመንገድ ትራፊክ አደጋ በአሽከርካሪዎች ጥፋትና የብቃት ማነስ መሆኑን በጥናቱ አመላክተዋል።

ጥናቱ የተካሄደው በኦሮሚያ፣አማራ፣ ትግራይ፣ ደቡብ ክልሎችና በአዲስ አበባ አስሩም ክፍለ ከተሞች እንደሆነ  አቶ ታምሩ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም