ራያ ዩኒቨርስቲ የባቄላና አተር ምርጥ ዘር እጥረት ለማቃለል የማባዛት ስራ እያካሄደ ነው

60

ማይጨው ጥቅምት 18/2013 (ኢዜአ) ራያ ዩኒቨርስቲ የባቄላና አተር ምርጥ ዘር እጥረት ለማቃለል አፍሪካ ራይዝንግ ከተባለ መንግስታዊ ካልሆነ ድርጅት ጋር በመተባባር የማባዛት ስራ እያካሄደ መሆኑን ገለጸ።

ምርጥ ዘሩ ከመኸሩ ወቅት ጀምሮ እየተባዛ ባለበት ትግራይ ደቡባዊ ዞን ያለበትን ደረጃ ለመገምገም የተዘጋጀ የመስክ ምልከታ ተካሄዳል።

በዚህ ወቅት በራያ ዩኒቨርስቲ የኢንዱስትሪ ቴክኖሎጂ ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር ተስፋይ ጎደፋይ ለኢዜአ እንዳሉት የባቄላና አተር ዘር ከድርጅቱ ጋር በጋራ  እያባዙ ያሉት በዞኑ ጥራጥሬ  አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች ነው።

የሚባዘው ዘር  የተሻለ ምርት ከመስጠቱ  በተጨማሪ  የመሬት ለምነት በመጠበቅ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።

አርሶ አደሮችን በማሳተፍ እየተካሄደ  ይሄው  ምርጥ የባቄለና አተር ዝርያ  በተሻለ ዋጋ በመሸጥ ጭምር  ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲው ዝርያው በበሽታ እንዳይጠቃ ክትትል ከማድረግ በተጨማሪ አርሶ አደሮች በኩታ ገጠም በማደራጀት  ወደ ሌሎች አካባቢዎች   የማስፋት ሀላፊነት ወስዶ ይሰራል ብለዋል።

በአፍሪካ ራይዝንግ ፕሮጀክት የደቡባዊ  ዞን  አስተባባሪ አቶ መሐመድ ኢብራሂም  በበኩላቸው በበሽታና ሌሎች  ችግሮች ምክንያት  የባቄላ እና አተር የዘር  አቅርቦት እጥረት ማጋጠሙን ገልጸዋል።

ችግሩን ለማቃለል ፕሮጀክቱ የተሻሻለ የባቄላና አተር ምርጥ ዘር በእምባ አላጀ ወረዳ ዓይባ ቀበሌ በኩታ ገጠም  ለተደራጁ  ከ60 በላይ አርሶ አደሮች በመስጠት በ13 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት የማባዛት ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ዝርያው በምርምር ጣቢያ በሄክታር እስከ 40 ኩንታል ምርት በመስጠት ከነባሩ በእጥፍ ብልጫ እንዳለው መረጋገጡን አስረድተዋል።

በቀጣይ የምርት ዘመን  በዞኑ በሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች ለማስፋት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ምርጥ ዘሩን ወስደው እያባዙ ከሚገኙ  የአላጀ ወረዳ አይባ ቀበሌ  አርሶ አደሮች መካከል አቶ ሀፍቶም ተቋረ በሰጡት አስተያየት ከሚባዙት ዘር የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ ገልጸዋል።

"ከአሁን በፊት እንዘራው የነበረው ባቄላ በበሽታ እየተጠቃ በመምጣቱ መዝራት አቁመን ነበር አሁን ግን የተሻለ ዘር ስላገኘን የተሻለ ምረት እንጠብቃለን" ብለዋል።

በመስክ ምልከታው የአካባቢው አርሶ አደሮች ፣ የዩኒቨርሲቲውና የድርጅቱ ተወካዮች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም