ህብረተሰቡ የደረሰ ሰብልን ከመሰብሰቡ በተጓዳኝ የመስኖ ልማት ለማካሄድ ጥረት እየተደረገ ነው

475

ደብረብርሃን ጥቅምት 18/2013 (ኢዜአ) የአንበጣ መንጋ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ከመከላከልና የደረሰ ሰብልን ከመሰብሰቡ በተጓዳኝ የመስኖ ልማትም ለማካሄድ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ። 

በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሄረሰብ አሰተዳደርና  ሰሜን ሸዋ ዞን የተወጣጡ ከ300 በላይ በጎፈቃደኛ ወጣቶች ትናንት በአንኮበር ወረዳ የደረሰ ሰብል ሰብስበዋል።

የግብር ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አይናለም ንጉሴ በሰብል አሰባሰቡ ሂደት ወቅት እንዳሉት ሰብላቸው በአንበጣ መንጋ  የተጎዳባቸው አርሶ አደሮችን ለመደገፍ በበጋ መስኖ በማሳተፍ  የተቀናጀ ርብርብ ማድረግ ይገባል።

ሚኒስቴሩ የአንበጣ መንጋ ጉዳት ባደረሰባቸው አካባቢዎች ሁሉንም የውሃ አማራጮች ተጠቅሞ በመስኖ ለማልማት አቅዶ በጋራ ለመተግበር ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ህብረተሰቡም በአንበጣ መከላከልና የደረሰ ሰብልን በመሰብሰብ ያሳየውን ተነሳሽነት በመስኖ ልማት በመድገም እንዲያግዝ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ከዚህ አንጻር በሰሜን ሸዋ  አጎራባች ዞኖችና ወረዳዎች የሚገኙ በጎ ፈቃደ ወጣቶች እያሳዩት ያሉት ትብብር ለቀጣይ የመስኖ ስራ የሚያገለግል አርአያነት ያለው ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።

የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ ሀላፊ ወይዘሮ መሰረት ሐይሌ በበኩላቸው  በአንበጣ  መንጋ  ሊከሰት የሚችለውን የምርት መቀነስ ለማካ ካስ  በዞኑ  28 ሺህ ሄክታር  መሬት ላይ የማልማት ስራ መጀመሩን አሰታውቀዋል።

የአንበጣ መንጋው በዞኑ  12 ወረዳዎች  በሚገኝ 93ሺህ  ሄክታር መሬት ላይ ቢከሰትም ከዚህ ውስጥ 86 በመቶው በሰው ሀይልና አውሮፕላን   በመታገዝ  መከላከል  መቻሉን  ገልጸዋል።

በጤፍና ማሽላ ሰብል ላይ የተወሰነ ጉዳት መድረሱን ጠቁመው  የአንበጣ መንጋው አሁን  ላይ የመቀነስ አዝማሚያ ቢያሳይም ማህበረሰቡ ሳይዘናጋ የደረሱ ሰብልን ፈጥኖ  እንዲሰበስብ አሳስበዋል።

የአማራ ክልል ሴቶች ወጣቶችና ህፃናት ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ አባይነህ መላኩ እንዳሉት ትናንት ከሰሜን ሸዋ፣ኦሮሞ ብሄረሰብ  አስተዳደርና መስሪያ  ቤቶች  የተውጣጡ ከ300 በላይ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን በሰብል መሰብሰብ ማሳተፍ ተችሏል።

የአንበጣ መንጋው ከተከሰተ ማግሰት ጀምሮ ወጣቱ  በመከላከል ስራው በንቃት በመሳተፍ የበኩሉን  መወጣቱን ጠቁመው አሁንም  አጋርነቱን እያሳየ መሆኑን ተናግረዋል።

ከኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር   ባቲ ወረዳ በምርት አሰባሰቡ ከተሳተፉት መካከል  ወጣት ሁሴን አህመድ በሰጠው አስተያየት በምርት አሰባሰቡ አጋጣሚ ከተለያዩ አካባቢ ከመጡ ሰዎች ጋር መገናኘታቸው በቀጣይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በጋራ ተጋግዘው ለመፍታት ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው ገልጿል።