የአሜሪካው ፕሬዚዳንት የጥፋት መልዕክት ከመሪነት ስነ ምግባር ያፈነገጠ መሆኑን ምሁራን ገለጹ

57

ባህርዳር ጥቅምት 182013 (ኢዜአ) የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን አስመልክተው ሰሞኑን ያስተላለፉት የጥፋት መልዕክት ከመሪነት ስነ ምግባር ያፈነገጠ መሆኑን በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።

ፕሬዚዳንቱ ሃላፊነት የጎደለውና በቀጠናው ጦርነትን ያወጀ ጠብ አጫሪ ንግግር በመሆኑ ሁሉም ህዝብ ሊያውግዘው እንደሚገባም  ምሁራኑ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ አመልክተዋል።

በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር አቶ ቻላቸው ታረቀኝ  እንዳሉት  የኢትዮጵያና አሜሪካ ግንኙነት ከ110  ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ነው።

በአጼ ሚኒሊክና ፕሬዚዳንት ሩዝቬልት የተጀመረው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በኢኮኖሚ፣  ደህንነት፣ ጤና፣ ትምህርትና ሌሎች ዘርፎች እስካሁን መልካም ሆኖ መዝለቁን አውስተዋል።

አሁን ላይ ኢትዮጵያ የመልማት መብቷን ተጠቅማ  ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ከመገንባቷ ጋር ተያይዞ ትራምፕ “ግብጽ ግድቡን ልታፈነዳው ትችላለች” በሚል ያስተላለፉት የጥፋት መልዕክት ከመሪነት ስነ ምግባር ያፈነገጠና ጸብ አጫሪነት መሆኑን ምሁሩ ገልጸዋል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በሀገራት ውስጥ  ጣልቃ ያለመግባትና ቅኝ ግዛትን ያለመደገፍ የሚለውን መርህ የጣሰ ነው ብለዋል።

በተለይም "እኛ ያቀረብነውን ስምምነት መፈረም ነበረባት፤ ባለመፈረሟ እስከመጨረሻው እርዳታ አታገኝም" በሚል የገለጹት ሃሳብ በእጅ አዙር የቅኝ ግዛቱን እኔ አውቅልሃለሁ አስተሳሰብ የተንጸባረቀበት በመሆኑ ተቀባይነት የለውም  ሲሉም ገልጸዋል።  

የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ድንጋጌ  ውስጥ  "የእያንዳንዱ አገር ዜጋ የኑሮ ደረጃውን የማሻሻል መብት አለው" የሚለውን የጣሰ ነው።

በድንጋጌው እንደተመላከተው እያንዳንዱ ሀገር ዜጋ ከትምህርት፣ ጤና፣ ምግብ፣ ውሃ ከማግኘት ባሻገር እንደ መብራትና ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን የማግኘት መብት ያለው ነው።

የፕሬዚዳንቱ መልዕክት  የአሜሪካን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲንና የተባበሩት መንግስታት ድንጋጌን የጣሰ በመሆኑ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ መላ የዓለም ህዝብ ሊያወግዘው ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብም በብሄር፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖትና በሌሎች ምክንያቶች እርስ በእርስ ከመናቆር በመውጣት ከአባቶቹ ታሪክ ተምሮ በአንድነት በመሰለፍ የውጭ ጣልቃ ገብነትን መመከት እንዳለበትም አመልክተዋል።

መንግስት በሀገር ውስጥ የሚገኙ ልዩነት ያላቸው አካላት  ወደ ሰላማዊ መንገድ በማምጣት ለህግ የበላይነትና ጠንካራ ሀገር ለመገንባት መስራት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።

ሌላው የህግ መምህሩ ረዳት ፕሮፌሰር ዘውዱ መንገሻ በበኩላቸው የፕሬዚዳንቱ የጥፋት መልዕክት  ከዓለም አቀፍ ህግና ዲፕሎማሲ መርህ አንጻር ሲታይ ፍጹም ተጻራሪ መሆኑን ገልጸዋል።

ፕሬዚዳንቱ ወደ ስልጣን እንደመጡ ከጎረቤቶቻቸው ሜክስኮና ካናዳ ጋር የነበራቸውን ልዩ የንግድ ልውውጥና የገበያ ትስስር እንዲቆም ማድረጋቸው በማሳያነት ጠቅሰዋል።

ሀገራት በራሳቸው  የሚያከናውኑት የልማት ተግባራት የሉአላዊነት መብታቸውን ተጠቅመው መሆኑ እየታወቀ የፕሬዚዳንቱ  ሀሳብ  የኢትዮጵያን ሉአላዊነት የተዳፈረ ነው ብለዋል።

የጸጥታው ምክር ቤት አባል የሆነች ሀገር መሪ “ግብጽ ግድቡን ልታፈነዳው ትችላለች” የሚል ንግግር መሰማቱ የዓለም አቀፍ ህግን የዲፕሎማሲ መርሆ የጣሰ መሆኑን አስረድተዋል።

በአሜሪካ ሲካሄድ በነበረው ድርድር ኢትዮጵያ ጥቅሜን ይጎዳል ብላ በመውጣቷ ፕሬዚዳንቱ ለምን ተደፈርን ዓይነት ቂም እንደያዙ ባስተላለፉት መልዕክት መረዳት ይቻላል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ግድቡን የምትገነባው በሀገር ውስጥና  ቀጠናው የሚስተዋለውን ከፍተኛ የሃይል እጥረት ለማቃለል የጀመረችው  እንጂ ማንንም ለመጉዳት እንዳልሆነ በተደጋጋሚ  ገልጻለች።

በዚህም ከ80 በመቶ በላይ ለናይል ወንዝ ውሃ የምታመነጭ ኢትዮጵያ  ፍትሃዊና ጉልህ ጉዳት ያለማደረስ በሚለው ዓለም አቀፍ ስምምነት ተመስርታ በአፍሪካ ህብረት የተጀመረውን ድርድር ማስቀጠል እንደሚገባም ምሁራኑ ጠቁመዋል።

በዚህም መላ ኢትዮጵያውያን ፕሬዚዳንት ትራንፕ በመጪው ምርጫ እንዳይመረጡ ከሌሎች ጥቁር ህዝቦች  ጋር በመተባበር መስራት እንዳለባቸው  መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም