ዱራቢሊስ የተሰኘ ዓለም አቀፍ ላኪ ድርጅት የኢትዮጵያን አቮካዶ ለውጭ ገበያ ማቅረብ ጀመረ

131

ጥቅምት 18/2013 (ኢዜአ) ዱራቢሊስ የተባለው ዓለም አቀፍ ላኪ ድርጅት በኢትዮጵያ የተመረተን አቮካዶ ለመጀመሪያ ጊዜ በተሳካ ሁኔታ ለውጭ ገበያ ማቅረብ መጀመሩን አስታወቀ።

ድርጅቱ የሙከራ ምርቶቹን መላክ የጀመረው የመጀመሪያውን ያለፈው መስከረም ወር እንዲሁም ሁለተኛውን ደግሞ በተያዘው ጥቅምት ወር መጀመሪያ ነው ተብሏል።

በዚህም ከደቡባዊ የባህር ዳር አካባቢ ከሚገኘው ቆጋ ቪሌጅ የግብርና ልማት እና በአካባቢው ከሚገኙ አነስተኛ አምራቾች የተገኙ ፍሬሽ የአቮካዶ ምርቶችን ለእንግሊዝ ገበያ ማቅረቡን አስታውቋል።

በዓለም አቀፍ የጥራት ተቆጣጣሪ አካል ፈቃድ የተሰጠው የአቮካዶ ምርት በእንግሊዝ ለሚገኙ ሁለት ግዙፍ አስመጪ ድርጅቶች እንዳስረከበ ሆርቲ ዴይሊ በድረገጹ አስነብቧል።

በተመሳሳይ ሁለት የሙከራ አቅርቦቶችን በቤልጂየምና ኔዘርላንድስ ከሚገኙ ደንበኞች ትዕዛዝ እንደቀረበለትና ሌላ ሁለት የሙከራ አቅርቦት ለተባበሩት አረብ ኤሜሬቶችና ሳዑዲ አረቢያ መጓጓዙን የካምፓኒው ሀላፊ ኤቨርት ዎልፍራንክ ገልጸዋል።

ሀላፊው አክለውም በኢትዮጵያ ያለውን የግብርና ልማት ዕምቅ አቅም ግምት ውስጥ በማስገባት በአቮካዶ ምርት የተጀመረውን ለውጭ ገበያ የማቅረብ ሂደት ውጤታማነት በማየት ለሌሎች የአውሮፓ ገበያ መቅረብ የሚችሉ የግብርና ምርቶችንም መላክ እንደሚጀምሩ ገልጸዋል።

ለዚህም በመኪና ከ2 እስከ 3 ቀናትን ጉዞ ከሚጠይቀው ይልቅ ቋሚ የምልልስ ጊዜን ጨምሮ አስተማማኝ ማቀዝቀዣ ያለውና በ30 ሰዓታት ውስጥም ምርቶችን ጅቡቲ ወደብ ማድረስ የሚችልና 750 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው የባቡር ትራንስፖርት መሰረተ ልማት ምርቶችን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ትልቅ አማራጭ መሆኑን ገልጸዋል።  

በአጠቃላይ ምርቶችን ከኢትዮጵያ አንስቶ አውሮፓ ገበያ ለማድረስ 30 ቀናትን የሚፈጅ መሆኑና በቀጣይ ይህንን የጊዜ ቆይታ ወደ 24 ሰዓት ማሳጠር የሚያስችል ዕድል እንዳለም በመረጃው ተገልጿል።

እንደ ሀላፊው ገለጻ ድርጅቱ ለማምረት ካቀደው የምርት ብዛት አንጻር በእንግሊዝ፣ በአውሮፓና በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ ተጨማሪ ተቀባዮችን እያነጋገሩ ሲሆን፤ ይህም ለገዥዎች ፍሬሽ ፍራፍሬና አትክልት አቅርቦት ተጨማሪ አማራጭ ዕድል ይፈጥርላቸዋል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ለምለም አፈሯ፣ ምቹ የአየር ባጸይ፣ በርካታ የውሃ አቅርቦቷና አንጻራዊ የሰራተኛ ክፍያ አመቺ መሆኑ በግብርናው ዘርፍ መልማት የሚችል ሰፊ አቅም እንዳላት ሀላፊው መግለጻቸውን መረጃው አስታውሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም