ማህበሩ በፈጥኖ ደራሽ የጥበቃና የጽዳት አገልግሎት ዘርፍ የሰለጠኑ አባላትን ዛሬ አስመረቀ

122

አዲስ አበባ ጥቅምት  17/2013 (ኢዜአ) የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት ድጋፍና የልማት ማህበር በፈጥኖ ደራሽ የጥበቃና የጽዳት አገልግሎት ዘርፍ የሰለጠኑ አባላትን ዛሬ አስመረቀ።

ለምረቃ የበቁት ቁጥራቸው 300 የሚሆኑ የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት ሲሆኑ በተለያዩ የመንግስትና የግል ድርጅቶች እንዲሁም  ኤጀንሲዎች ውስጥ በጥበቃ እና በተለያዩ የሥራ ዘርፎችፍ ተቀጥረው መስራት የሚችሉ ናቸው ተብሏል።

የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት የድጋፍና የልማት ማህበር ፕሬዚዳንት ሃምሳ አለቃ ብርሃኑ አማረ በዚህ ወቅት እንዳሉት፣ ሠራዊቱ ከዚህ ቀደም አገሩን በትጋት ያገለገለ መሆኑን አስታውሰዋል።

ሆኖም ላለፉት በርካታ ዓመታት ትኩረት ተነፍጎት የቆየ በመሆኑ የሠራዊቱ አባላት በከፍተኛ ውጣ ውረድና ችግር ውስጥ ማሳለፋቸውን ተናግረዋል።

"ከሁለት ዓመታት በፊት የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት የድጋፍና የልማት ማህበር መቋቋሙን ተከትሎ  ማህበሩ የሠራዊቱ አባላት የሚገባቸውን ድጋፍ እዲያገኝ እየሰራ ነው" ብለዋል።

የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት በአሁኑ ወቅት በርከታ ተግባራትን እያከናወኑ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የማህበሩ ሥራ አስፈጻሚ አባል መቶ አለቃ ታሪኩ በቀለ ናቸው።

በአሁኑ ወቅት ካለው የአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት ጋር  አገርን በማልማት ሥራ በጋራ እየሰሩ መሆናቸውንና በቀጣይም በኢትዮጵያ ሰላም፣ ልማትና እድገት ላይ የድርሻቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።

በእለቱ በአሜሪካን አገር የሚኖሩ ትውልደ አትዮጵያዊ አቶ ሰለሞን ገብረማሪያም ለቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊቱ አባላት 250 የደምብ ልብሶችን  ወዳጆቻቸውን በማስተባበር ድጋፍ አድርገዋል።

ለአገር ባለውለታዎች እንዲህ ያሉ ድጋፎችን ማድረግ ተገቢ መሆኑን ገልጸው፣ በቀጣይም ማህበሩን በተለያዩ መንገዶች ለመደገፍ የማስተባበር ሥራቸውን እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት ድጋፍና የልማት ማህበር ከተመሰረተ ሁለት ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን በመላው አገሪቱ 274 ቅርንጫፎች እና 1 ሚሊዮን አባላት እንዳሉት ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም