ሦስት የረድኤት ተቋማት ለጤና ሚኒስቴር የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ

72

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17/2013 ( ኢዜአ) ሦስት የረድኤት ተቋማት ኮሮና ቫይረስን ለመከላከልና ለቲቢ ሕሙማን ሕክምና ለመስጠት የሚያገለግሉ ግምታቸው 4 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ቁሳቁስ ለጤና ሚኒስቴር ድጋፍ አደረጉ።

ፓዝ የተሰኘው ዓለም አቀፍ የረድኤት ድርጅት 2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገባቸው የኮሮናቫይረስ መከላከያ ቁሶች ድጋፍ አድርጓል።

ድጋፉ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብሎች፣ ሳኒታይዘር ፣ ክሎሪን፣ የፈሳሽ ሳሙና፣ የእጅ ጓንት፣ የህክምና ጓንትና የፕላስቲክ ልብሶችን ያካተተ ነው።

ለጤና ሚኒስተር ድጋፉን ያስረከቡት የተቋሙ ተወካይ ወይዘሮ ትርሲት ግርሻው በቀጣይም ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።  

ብርቅዬ በጎ አድራጎት ድርጅትም 270 ሺህ ብር ወጪ የተደረገባቸው የሕክምና አልባሳትን በተወካዩ በአርቲስት ደበበ እሸቱ በኩል አስረክቧል።

አልባሳቱ ኮሮናቫይረስን ለመከላከል በግንባር ቀደምነት ለሚሰሩ የጤና ባለሙያዎች የሚውሉ ሲሆን ተቋሙ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አርቲስት ደበበ ተናግሯል።

የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጀት (ዩ ኤስ አይዲ) 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገባቸውና ለቲቢ በሽታ መመርመሪያ የሚውሉ ኬሚካሎችን ድጋፍ አድርጓል።

ድርጅቱ ቀደም ሲልም ቲቢን ለመከላከል ለወጣው የአምስት ዓመት ስትራቴጂ ሰነድ የቴክኒክ ድጋፍ ማድረጉንም የተቋሙ ተወካይ ዶክተር አስፋወሰን ገብረዮሐንስ ገልጸዋል።   

ሦስቱ የረድኤት ተቋማት ያደረጉትን ድጋፍ የተረከቡት የጤና ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ደረጄ ዱጉማ በበኩላቸው "ተቋማቱ ላደረጉት ድጋፍ አመስግነው፤ ድጋፉ ለጤናው ዘርፍ መጠናከር የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው" ብለዋል።

በተለይም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የአጋር አካላት እገዛ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው፤ በዛሬው ዕለት የተደረገው ድጋፍም የዚሁ ትብብር አካል መሆኑን ጠቁመዋል።

ከዚህ ቀደም ድጋፍ ያላደረጉ ተቋማት ድጋፍ እንዲያደርጉና ድጋፍ ያደረጉ ተቋማትም ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ ዶክተር ደረጄ ጠይቀዋል።

ህብረተሰቡም የኮሮናቫይረስ ስርጭት እየተስፋፋ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት ለወረርሽኙ ተጋላጭ እንዳይሆን ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም