ሁሉም አካል ለሠላም ግንባታ አበክሮ እንዲሰራ የኢትዮጵያ ሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠየቀ

65

ሀዋሳ ጥቅምት 17/2013 (ኢዜአ) የሀገሪቱ ህዝቦች የተጎናጸፉትን ማህበራዊ ዕሴቶች በማበልጸግ ለሠላም ግንባታ ሁሉም አካል አበክሮ እንዲሰራ የኢትዮጵያ ሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠየቀ።

ጉባኤው ለሃይማኖት መሪዎችና ባለድርሻ አካላት በሠላም ግንባታ ዙሪያ ያዘጋጀው ምክክር መድረክ  ዛሬ በሀዋሳ ከተማ  ተጀምሯል።

በዚህ ወቅት የጉባኤው ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉሀን ቀሲስ ታጋይ ታደለ እንዳሉት ከሁሉም በላይ ሠላም ከፈጣሪ የተሰጠን ጸጋ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው።

በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ በተለያየ መልኩ የሚከሰት የሠላም እጦት መንስዔው በሠላም ግንባታ ላይ   ተመርኩዘን ጠንክረን ባለመሥራታችን የተፈጠረ ችግር  ነው ብለዋል።

ይህ ችግር ስር ሳይሰድና ተጨማሪ ጉዳቶች ሳያስከትል ከወዲሁ ለመቆጣጠር እንዲቻል ሁሉም አካል ለሠላም ግንባታ አበክሮ እንዲሰራ ጠየቀዋል።

በዚህ ረገድ ከእያንዳንዱ የሐይማኖት ተቋማትና ሃይማኖተኛ ነኝ ከሚል ዜጋ ሐማኖታዊ ግዴታ    እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ጉባኤውም ሠላምን ሊያጠናክሩና የህዝቦችን ትስስር ሊያጎለብቱ የሚችሉ ምክክሮችንና ስልጠናዎችን የማዘጋጀት እንቅስቃሴውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተወካይ አቶ ተሰማ ዲማ  ዘላቂ ሠላም በማስፈን ረገድ ከጉባኤው ብዙ ይጠበቃል ብለዋል።

የተጀመረው የብልጽግና ጉዞ እንዲሳካ የመልማት ጥያቄዎች በጠንካራ የስራ ባህልና ሠላም እንዲታገዝ የሐይማኖት ተቋማት የተጣለባቸውን  ኃላፊነት እንዲወጡም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በመንግስት  በኩል ሃገር በቀል ዕውቀቶች በማካተት ሀገር ተረካቢ ወጣቶች ሁሉ አቀፍ ስብዕና ግንባታ ላይ ያተኮረ ሥርዓት ትምህርት እያዘጋጀ መሆኑን ጠቁመው ለዚህ እውን መሆን ሁሉም ሊረባረብ እንደሚገባ       አሳስበዋል።

በቀጣይም የክልሉ መንግስት ከሐይማኖት ተቋማት ጉባኤው ጋር ተባብሮ ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል።

ለሁለት ቀናት በተዘጋጀው መድረክ በሰላም ግንባታ ዙሪያ ከመምከር በተጨማሪ የሲዳማ ክልል የሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ ይመሠረታል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም