የኢትዮጵያ አየር መንገድ በምርጥ የአፍሪካ አየር መንገድ ዘርፍ የ2020 የንግድ ተጓዥ ሽልማት አገኘ

79

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17/2013 ( ኢዜአ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ በምርጥ የአፍሪካ አየር መንገድ ዘርፍ የ2020 የንግድ ተጓዥ ሽልማት አሸናፊ ሆነ።

ዋና መቀመጫውን በለንደን ያደረገው የንግድ ተጓዥ መጽሔት አሳታሚ "ፓናሴአ ሚዲያ" ኩባንያ የ2020 የንግድ ተጓዥ ሽልማቶችን ዛሬ ይፋ አድርጓል።

በዚሁ መሰረት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በምርጥ የአፍሪካ አየር መንገድ ዘርፍ የ2020 የንግድ ተጓዥ ሽልማት አሸናፊ መሆኑን ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

አየር መንገዱ የደቡብ አፍሪካ፣ኬንያና ሞሮኮ ብሔራዊ አየር መንገዶችን አሸንፎ ነው ሽልማቱን ማግኘት የቻለው።

"ፓናሴአ ሚዲያ" የተሰኘው ኩባንያ በ43 የተለያዩ ዘርፎች አሸናፊዎችን ይፋ ያደረገ ሲሆን፤ አሸናፊዎቹ የተመረጡት የንግድ ተጓዥ መጽሔት በሚያነቡ ሰዎች በሰጡት ድምጽ አማካኝነት መሆኑ ተገልጿል።

የመጽሔቱ አንባቢዎች የሰጡት ድምጽ ውጤት ያሳወቀው ገለልተኛ የሆነ የጥናት ኩባንያ መሆኑ ተመልክቷል።

የዘንድሮው ዓመት ሽልማት የንግድ ተጓዥ መጽሔት ከሚያዚያ እስከ ሐምሌ ወር 2012 ዓ.ም የመጽሔቱ አንባቢዎች ከተጠቀሰው ጊዜ በፊት በነበሩት 12 ወራት በነበራቸው የጉዞና የአገልግሎት ቆይታ ላይ ባደረገው የዳሰሳ ጥናት ላይ መሰረት ያደረገ መሆኑ የመጽሔቱ አዘጋጆች ገልጸዋል።

የዳሰሳ ጥናቱ የቆይታ ጊዜ በመጋቢት ወር 2012 ዓ.ም አገራት የኮቪድ-19 ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በስፋት የንግድ ጉዞዎች ላይ ገደብ ከመጣላቸው በፊት ያለውን ወቅት ነው።

የኳታር አየር መንገድ የዓመቱ ምርጥ አየር መንገድና የመካከለኛው ምስራቅ ምርጥ አየር መንገድ ዘርፍን ጨምሮ አምስት ሽልማቶች በማግኘት የቅድሚያውን ስፍራ ይዟል።

የብሪታኒያና ሲንጋፖር አየር መንገዶች በተመሳሳይ በአራት ዘርፎች ሽልማት አግኝተዋል።

የንግድ ተጓዥ መጽሔት የኤዲቶሪያል ዳይሬክተር ቶም ኦትሌይ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት አብዛኛው የንግድ ተጓዥ ቤቱ ሆኖ እየሰራበት ባለበት ሰአት ይህ ሽልማት መሰጠቱ አስደሳች መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም የንግድ ተጓዥ አሸናፊዎችና የመጨረሻ እጩ ተወዳዳሪዎች በወረርሽኙ ምክንያት ከባድ ጊዜ እያሳለፉ ባለበት ጊዜ መሆኑ የሽልማቱን ትርጉም ከፍ እንደሚያደርገው ገልጸዋል።

በሽልማቶቹ ላይ ለተሳተፉት በሙሉ ምስጋናቸውን ያቀረቡት ዳይሬክተሩ ቀጣዮቹ 12 ወራት ለሁላችንም መልካም ዜና ይዞ ይመጣል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም