የአስተዳደር ወሰን፣ የማንነትና ራስን በራስ የማስተዳደር ጉዳዮች ላይ የሚደረገው ጥናት በግንቦት ወር ይጠናቀቃል

150

አዲስ አበባ ጥቅምት 17/2013 (ኢዜአ) የአስተዳደር ወሰን፣ የማንነትና ራስን በራስ የማስተዳደር ጉዳዮች ላይ የሚደረገው አጠቃላይ አገራዊ የዳሰሳ ጥናት በመጭው ግንቦት ወር እንደሚጠናቀቅ የአስተዳደር ወሰንና ማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ገለጸ።

በክልሎች መካከል የአስተዳደር ወሰን ጥያቄ ያለባቸው ዞኖች፣ ወረዳዎችና ቀበሌዎች በጥናቱ ይካተታሉ ተብሏል። 

የአስተዳደር ወሰንና ማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን የ2013 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የሥራ ክንውኑን በተመለከተ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

የኮሚሽኑ ሰብሳቢ ዶክተር ጣሰው ገብሬ እንዳሉት ኮሚሽኑ በጥናት ላይ የተመሰረተ የማያዳግም የመፍትሄ ምክረ ሃሳብ ለማቅረብ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአዋጅ ቁጥር 1101/2011 የተቋቋመ መንግስታዊ ተቋም ነው።

"ኮሚሽኑ በአስተዳደር ወሰን፣ በማንነትና ራስን በራስ ማስተዳደር ጉዳዮች ላይ ጥልቅ ጥናትና ምርምር በማቅረብ ለመንግስት ምክረ ሃሳብ ያቀርባል" ብለዋል

ለዚህም ኮሚሽኑ አደረጃጀቱን ካስተካከል በኋላ ከሰኔ ወር 2012 ዓ.ም ጀምሮ ከአዲስ አበባ ዪኒቨርሲቲ ጋር የጥናትና ምርምር ውል መፈራረሙን ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ከ28 ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ከ70 በላይ ተመራማሪዎች የሚሳተፉበት አገራዊ ጥቅል የምርምር ሥራ 40 በመቶ መድረሱን ገልጸዋል።

"በመሆኑም ኮሚሽኑ የሚያስጠናው አጠቃላይ አገራዊ የዳሰሳ ጥናት እስከ ግንቦት 2013 ዓ.ም ድረስ ይጠናቀቃል" ብለዋል።

በክልሎች መካከል የአስተዳደር ወሰን ጥያቄ የሚነሳባቸው ዞኖች፣ ወረዳዎችና ቀበሌዎች በሙሉ በጥናቱ እንደሚካተቱም ዶክተር ጣሰው ተናግረዋል።

የአስተዳደር ወሰንና ማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ አወል ሁሴን በበኩላቸው "የአስተዳደር ወሰን የማንነትና ራስን በራስ የማስተዳደር ጉዳዮች ላይ  ዘላቂ መፍትሄ የሚመጣው  'አንተም ተው አንተም ተው' በሚል ሳይሆን በጥናት ላይ በተመሰረት ውጤት ነው" ብለዋል።

ለእዚህም ከ28 ዩኒቨርሲቲዎች የተመረጡ ከ70 በላይ ተመራማሪዎች ነጻና ገለልተኛ መሆናቸውን የሚያሳይ መስፈርት መውጣቱን ነው የተናገሩት።

"የሙያ ብቃት፣ የትምህርት ዝግጅት እና ልምድ እንዲሁም ነገሮችን ገለልተኛ ሆኖ የማየት አዝማሚያን ለመመልመያ መስፈር ተጠቅመናል" ብለዋል አቶ አወል።

ከዚህ በተጨማሪ ተመራማሪዎች ነጻና ገለልተኛ ሆነው መስራታቸውን ለማረጋገጥ በየጊዜው ሥራቸው እንደሚገመገም ነው ያስታወቁት  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም