የአዲስ አበባ ከተማ አሰተዳደር በሠዓሊ የክብር ዶክተር ሎሬት ለማ ጉያ ህልፈት የተሰማውን ሀዘን ገለጸ

72

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16/2013 ( ኢዜአ) የአዲስ አበባ ከተማ አሰተዳደር በሠዓሊ የክብር ዶክተር ሎሬት ለማ ጉያ ህልፈት የተሰማውን ሀዘን ገለጸ

አስተዳደሩ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው አንጋፋው ሠዓሊ ለማ ጉያ በተፈጥሯዊ አሳሳል ካበረከቷቸው ስራዎች መካከል "የሸክላ ገበያ" እና "የደንከል ልጃገረድ" በዋናነት ይጠቀሳሉ።

በቢሾፍቱ ከቤተሰቦቻው ጋር በመሆን "የአፍሪካ ሙዚየም" በሚል ባሰሩት የጥበብ ማዕከል ስራዎቻቸውን ሲያስጎበኙ ቆይተዋል።

በአፍሪካ ኅብረት ያገለገሉ ፀሐፊዎችን፣ በኦሮሚያ የባህል ማዕከል የኦሮሚያ ክልል ኘሬዚዳንቶችንና የኦሮሞ ባህልና ትውፊትን የሚያሳዩ የቆዳ ላይ ስዕሎችንም አበርክተዋል።

የክብር ዶክተር ሎሬት ለማ ጉያ ከአባታቸው ከአቶ ጉያ ገመዳና ከእናታቸውን ከወይዘሮ ማሬ ጎበና በቀድሞው ምስራቅ ሸዋ አደአ ሊበን ወረዳ ዳሎ ቀበሌ ሕዳር 1921 ዓ.ም ተወለዱ ።

አርቲስቱ በህክምና ሲረዱ ቆይተው በተወለዱ በ92 ዓመታቸው በዛሬው ዕለት ጥቅምት 16 ቀን 2013 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

አርቲስቱ ከ10 ሺህ በላይ ስዕሎችን በፍየል ቆዳ ላይ በመሳል አድናቆትን አትርፈዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አሰተዳዳር በታላቁ አርቲሰት ሞት የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን ገልፆ ለቤተሰቦቻቸውና ለመላው አድናቂዎቻቸው መጽናናትን ተመኝቷል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም