በቴሌኮም ዘርፍ የሚሳተፉ ተጫራቾችም ሆኑ የተቋቋመው ተቆጣጣሪ አካል ከሌብነት የፀዳ ስራ እንዲያከናውኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳሰቡ

149

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 16/2013 (ኢዜአ) በቴሌኮም ዘርፍ በጨረታ የሚሳተፍም ሆነ የተቋቋመው ተቆጣጣሪ አካል ከሌብነት የፀዳ ስራ እንዲያከናውኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አሳሰቡ።

በቴሌኮም ዘርፍ የማሻሻያ ስራዎች ሂደት ላይ ያተኮረ ውይይት ባለፈው ዓመት ወርሃ ጳጉሜ ተካሂዶ ከባለድርሻ አካላት ግብዓት እንዲሰበሰብና ተጨማሪ ውይይት እንዲደረግበት አቅጣጫ ተቀምጦ ነበር።

የኢትዮጵያ ኮሙዩኒኬሽን ባለስልጣን፣ ኢትዮ ቴሌኮምና የገንዘብ ሚኒስትር በየዘርፋቸው ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይተው ሪፖርት እንዲያቀርቡ አቅጣጫ መቀመጡ ይታወሳል።

በዚህም መሰረት በዛሬው እለት በቴሌኮም ዘርፍ የማሻሻያ ስራዎች ላይ ያተኮረ ውይይት በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ተካሄዷል፡፡

የኢትዮጵያ ኮሚዩኒኬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ባልቻ ሪባ በሪፖርታቸው ከባለድርሻ አካላት ቀርበዋል ያሏቸውን አንኳር ጉዳዮች አንስተዋል።

የቴሌኮም ዘርፍ ማሻሻያ ዋና ዋና የፖሊሲ አላማዎች ምንነት፣ የመሰረተ ልማት ግንባታና አቅርቦትን በተመለከተ፣ የጨረታ ሂደት፣ የፈቃድ ወሰንና የባለስልጣኑ የመቆጣጠር አቅምና ዝግጁነትን የተመለከቱ ጥያቄዎች መቅረባቸውን ጠቅሰዋል።

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ ኢትዮ ቴሌኮም በዘርፉ ከሚመጡ ኦፕሬተሮች ጋር ተወዳዳሪ፣ ብቁ እና ተመራጭ ሆኖ ለመገኘት የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ስለመሆናቸው አብራርተዋል።

ኢትዮ ቴሌኮም ያለውን መሰረተ ልማት በሊዝ በማከራየት በዓመት ከ1 ነጥብ 6 እስከ 1 ነጥብ 8 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ማስገባት እንደሚችል ተናግረዋል።

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ በበኩላቸው የቴሌኮም ዘርፍ ለውድድር ክፍት መሆኑ ለኢኮኖሚው አስተዋፆ እንዳለው ገልፀዋል።

ከባለድርሻ አካላት ጋር በተደረገ ውይይት የተለያዩ ግብአቶች መገኘታቸውን ጠቅሰው ትኩረት ይሰጥባቸው ያሏቸውን ነጥቦችም አንስተዋል።

በዚህም የተቆጣጣሪ ባለስልጣኑ የሰው ሃይል ማጎልበትና መሰረተ ልማት ላይ ለሚመጡ ኦፕሬተሮች የግንዛቤ ማስጨበጫና የህዝብ ግንኙነት ስራዎች መሰራት እንዳለባቸው አንስተዋል።

ከጨረታ፣ ከፖሊሲ፣ የስራ አጥነት ችግርን ከማቃለል አንፃር፣ የሚመጡ ኦፕሬተሮች ተደራሽነት፣ ከብሄራዊ ደህንነት እና ከተቆጣጣሪ ባለስልጣን አቅም ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችንም የውይይቱ ተሳታፊዎች አንስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በሰጡት የማጠቃለያ ሃሳብ ይህን ዘርፍ ጠንካራ የሚቆጣጠር አካል ከሌለ ስራውን ማከናወን ያስቸግራል ብለዋል።

ስራው ከተጀመረ 2 ዓመታት እንደሆነው ጠቅሰው ስራው የቆየበት ዋነኛ ምክንያትም ጠንካራ ተቆጣጣሪ ተቋም ግንባታ ላይ አተኩሮ ለመስራት መሆኑን ገልጸዋል።

የቴሌኮም ዘርፍ የማሻሻያ ስራዎች የተፈለገው ኢኮኖሚውን ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚ እንዲያሸጋግር በመሆኑ በዘርፉ የሚኖረው ውድድር የተሻለ አዳዲስ አገልግሎትና ፈጠራ እንዲኖር ያደርጋል ብለዋል።

ከጨረታ ጋር ተያይዞ ለቀረበ ጥያቄ በሰጡት ምላሽም ጉዳዩ ተራ ሌብነት የሚፈፀምበት እንዳልሆነና የቢሊዮን ዶላሮች ግብይት በመሆኑ ጥንቃቄ በማስፈለጉ የጨረታ ሂደቱ እንዲዘገይ መደረጉን ተናግረዋል።

በቴሌኮም ዘርፍ በጨረታ የሚሳተፍም ሆነ የትኛውም ተቆጣጣሪ አካል ከሌብነት የፀዳ የኢትዮጵያን ህዝብ የማያሳፍር ስራ እንዲሰሩ አሳስበዋል።

በሂደቱ የጥቅም ግንኙነት እንዳይኖር ተገቢው ጥንቃቄ እና ቁጥጥር ይደረጋልም ብለዋል።

ዘርፉ ሰፊ የሰው ሃይል መቅጠር የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰው የሚደረገው ማሻሻያ ብሄራዊ ጥቅምን ያስጠበቀ እና የሚፈለገውን ውጤት የሚያመጣ እንደሆነ ገልፀዋል።

ከብሄራዊ ደህንነት አንፃርም ጥቃት ቢፈፀም መከላከል እንዲያስችል በርካታ ተቋማት እንዲጠናከሩ መደረጉንና ጥቃቶችን መከላከል የሚያስችል የተቋማት ዝግጅት መኖሩን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም