በመጪው ረቡዕ በአማራ ክልል ከተሞች ይካሔዳል የተባለው ሰልፍ እውቅና የለውም…የክልሉ መንግስት

69

ባህርዳር ጥቅምት 16/2013 (ኢዜአ) በአማራ ክልል በዚህ ሳምንት በተለያዩ ከተሞች ሊካሄድ የታሰበው ሰላማዊ ሰልፍ በክልሉ መንግስት እውቅና የሌለው መሆኑን የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

የጽሕፈት ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ማምሻውን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት በተለያዩ ከተሞች ጥቅምት 18/2013 ዓ.ም ሰላማዊ ሰልፎች እንደሚካሄዱ በማህበራዊ ድረ-ገጾች እየተናፈሰ ይገኛል።

"ይሁን እንጂ ይካሄዳል ለተባለው ሰልፍ አስከ አሁን ድረስ ህጋዊ ደብዳቤ ያስገባ አካል ባለመኖሩ ህገ-ወጥና እውቅና የሌለው ነው" ብዋል።

ሰልፉ በክልሉ ላይ አለመረጋጋት ለመፈጠር አቅደው እየሰሩ ላሉ አካላት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር እንደሆነም ዳይሬክተሩ በመግለጫቸው አስታውቀዋል።

"በኢትዮጵያ የመጣው ለውጥ እንዳይቀጥል የሚፈልጉ አካላት በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደረውን የአማራ ህዝብ ማህበራዊ እረፍት በመንሳት ለውጡን ለማደናቀፍ እየሰሩ እንደሚገኙ ሁሉም ማወቅ አለበት" ብለዋል።

"የክልሉ መንግስት የሰጠውን መግለጫ በመተላለፍ ወደ ሰልፍ የሚወጡ አካላት ካሉ የጸጥታ አካላት ህግ የማስከበር ሃላፊነታቸውን ይወጣሉ" ብለዋል።

በክልሉ ተወላጆች ላይ እየደረሰ ያለውን ችግር ለመከላከል የክልሉ መንግስት በህግ አግባብ እየሰራ መሆኑን ህዝቡ ተገንዝቦ እንደዚህ ላለ ህገ-ወጥ ተግባር ተባባሪ እንዳይሆን ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም