በሀዋሳ ድንገተኛ የእሳት አደጋ ንብረት ላይ ጉዳት አደረሰ

731

ሐዋሳ፤ጥቅምት 16/2013(ኢዜአ) በሀዋሳ ከተማ አሮጌ ገበያ ትናንት ሌሊት በደረሰ ድንገተኛ የእሳት አደጋ በ32 ሱቆች ላይ ጉዳት ማድረሱን ፖሊስ አስታወቀ። 

የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ መምሪያ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኢንስፔክተር ግርማ አብሽሮ ለኢዜአ እንደተናገሩት የእሳት አደጋው የደረሰው ትናንት ሌሊት ከምሽቱ 7 ሰዓት አካባቢ  ነው።

በዚህም በ32 ሱቆች ውስጥ የነበረ የሸቀጣ ሸቀጥ ምርት ሙሉ በሙሉ መውደሙን አስታውቀዋል፡፡

የአደጋው መንስኤና የደረሰው የንብረት ጉዳት ግምት የሚለይ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ስራ መገባቱን ጠቁመዋል።

የከተማዋ አስተዳደር የእሳት አደጋ መከላከያ ብርጌድ ከሀዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ የእሳት አደጋ መከላከያና መቆጣጠሪያ ብርጌድ ጋር በመተባበር ባደረጉት ርብርብ ቃጠሎው ሳይስፋፋ መቆጣጠር መቻሉን ኢንስፔክተሩ ገልጸዋል።