በገላና ወረዳ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመደገፍ ጥረት እየተደረገ ነው

156

ነገሌ፣ ጥቅምት 16/2013 (ኢዜአ ) በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን ገላና ወረዳ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመደገፍ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የወረዳው አደጋ ስጋት ስራ አመራር ጽህፈት ቤት ገለጸ።

የወረዳው አደጋ ስጋት ስራ አመራር ጽህፈት ቤት ኃላፊ ተወካይ አቶ ድጋፌ ዘሪሁን እንዳሉት ሰሞኑን ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ  ያስከተለው ጎርፍ በወረዳው 16 የገጠር ቀበሌዎች 37 ሺህ የሚጠጋ የቤተሰብ አባላትን አፈናቅሏል።

በ1 ሺህ 429 ሄክታር መሬት ላይ በተዘራ ሰብል፣ በ5 ሺህ 189 የመኖሪያ ቤቶችና 7 ትምህርት ቤቶች ላይ ጉዳት ማድረሱን ተናግረዋል።

በግብርናው ዘርፍ ጉዳት ከደረሰባቸው ሰብሎች መካከል በዋናነት የቡና ልማት፣ ጤፍ፣ ድንች፣ ስንዴና  ገብስ  ይገኙበታል፡፡

ተፈናቃዮቹ በአሁኑ ወቅት በወረዳው በሚገኙ በተለያዩ በጊዜያዊነት በተቋቋሙ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ተጠልለው እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡

ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተገኘ የምግብ እህል፣ የቀንና የሌሊት አልባሳት በማቅረብ ለመደገፍ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አቶ ድጋፌ ገልጸዋል፡፡

በወረዳው የሜጣሪ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ለገሠ ገልገሌ በሰጡት አስተያየት ጎርፉ የመኖሪያ ቤታቸውንና በማሳ ላይ የነበራቸውን ሰብል እንዳጠፋባቸው  ተናግረዋል፡፡

በዚህም ምክንያት ከነቤተሰባቸው ለችግር ተጋልጠው  ድጋፍ ጠባቂ ለመሆን መገደዳቸውን ገልጸዋል፡፡

ሌላው ነዋሪ  አቶ ገዳ ወንጀላ በበኩላቸው የጎርፍ አደጋው በድንገት የተከሰተ በመሆኑ በንብረታቸው ላይ ያልጠበቁት ጉዳት እንዳደረሰባቸው መናገራቸውን የዞኑን ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም