በአንበጣ መንጋ ሰብላቸው ለወደመባቸው አርሶ አደሮች አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል-- ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ

90

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 15/2013 ( ኢዜአ) በአንበጣ መንጋ ሰብላቸው ለወደመባቸው አርሶ አደሮች አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ።

እስካሁን ባለው ሂደት የአንበጣ መንጋውን 79 በመቶ መቆጣጠር መቻሉንም ጨምረው ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን የተናገሩት በደቡብ ወሎ ዞን ወረባቦ ወረዳ በአንበጣ መንጋ የተጎዱ የሰብል ማሳዎችን ዛሬ በጎበኙበት ወቅት ነው።

በጉብኝቱ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እና የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተመስገን ጥሩነህን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችም ተገኝተዋል።

አርሶ አደሮች በዚህ ወቅት የአንበጣ መንጋው ከዚህ ቀደም ባልተለመደ መልኩ በደረሱ ሰብሎቻቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ተናግረዋል።

አርሶ አደር ይማም መሀመድ የወረዳው አመራሮችና የአካባቢው ማህበረሰብ አንበጣውን ለመከላከል በመኪና የታገዘ የኬሚካል ርጭትን ጨምሮ ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም ከአንበጣው ስፋት አንጻር የታሰበውን ያህል ውጤት ማምጣት እንዳልተቻለ ነው የገለጹት።

በክረምት ወቅት የለፉበት ሰብል ሙሉ ለሙሉ መውደሙን የጠቆሙት አርሶ አደሩ፤ በአሁኑ ወቅት ከእነቤተሰቦቻቸው ችግር ውስጥ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በመሆኑም መንግስት ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ነው ጥሪ ያቀረቡት።

የወረባቡ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አሊ መሀመድ በበኩላቸው ወረዳው ካለው 20 የገጠር ቀበሌዎች ውስጥ የአንበጣ መንጋው በ13 ቀበሌዎች ላይ ጉዳት ማድረሱን ተናግረዋል።

በዚህም ከ62 ሺህ በላይ የወረዳው ነዋሪዎች ለችግር መዳረጋቸውን ነው ያመለከቱት።

የፌደራል መንግስት ለእነዚህ ዜጎች ከሚያደርገው ድጋፍ በተጨማሪ በአካባቢው ያለውን የመስኖ አቅም መጠቀም በሚቻልበት ላይ ትኩረት እንዲያድርግም ጥሪ አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ በበኩላቸው የአንበጣ መንጋው በሀገር አቀፍ ደረጃ በ700 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ በለማ ሰብል ጉዳት ማድረሱን ጠቁመዋል።

መንግስትና የአካባቢው ማህበረሰብ ጉዳቱ ይበልጥ እንዳይሰፋ በቅንጅት ያከናወኑትን ተግባርም አድንቀዋል።

እስካሁን ባለው ሂደትም 79 በመቶ የሚሆነውን የአንበጣ መንጋ መቆጣጠር መቻሉን ጠቅሰው፤ ቀሪውን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል።

በቀጣይ ሰብሎቻቸው ለወደሙባቸው አርሶ አደሮች አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ በመጠቆም።

በጉብኝቱ ጉዳት ለደረሰባቸው አርሶ አደሮች መንግስት ምን አይነት እገዛ ማድረግ እንዳለበት መገንዘባቸውን የገለጹት ዶክተር ዐቢይ፤ ኢትዮጵያዊያን በጋራ በመቆምና በመተጋገዝ የተፈጥሮም ሆኑ ሌሎች አደጋዎች የአገር ስጋት እንዳይሆኑ ሚናቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።

በዘንድሮው ዓመት ከ35 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ትርፍ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታውሰው፤ ከዚህ አንጻር የአንበጣ መንጋው በአገር አቀፍ ምርት ላይ የሚያደርሰው ተጽዕኖ ጥቂት ሊሆን እንደሚችል አመልክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁንም ያለምንም መዘናጋት የደረሱ ሰብሎችን ከአንበጣና ሌሎች ጥቃቶች መከላከል እንደሚገባ ነው ያስጠነቀቁት።

በአሁኑ ውቅት በአንዳንድ አካባቢዎች የወፍ መንጋ እየታየ በመሆኑ ጥንቃቄ እንዲደረግም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሳስበዋል።

በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ወረባቦ ወረዳ የአንበጣ መንጋ ወረርሽኝ 9 ሺህ ሄክታር የማሽላ ሰብል በማውደሙ አርሶ አደሩ ለችግር መጋለጡ ከዚህ በፊት የዞኑ ግብርና መምሪያ ለኢዜአ መግለጹ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም