በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ተቋማዊ የለውጥ ጉዞ እንዲሳካ የላቀ አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት እውቅና ተሰጠ

85

ዲላ፣ ጥቅምት 14/2013 (ኢዜአ) በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ተቋማዊ የለውጥ ጉዞ ለማረጋገጥ በተደረገው ጥረት የላቀ ሚና ላበረከቱ አካላት እውቅና ተሰጠ።

ዩኒቨርሲቲው ባዘጋጀው  መድረክ እውቅናና የተሰጠው ለተቋሙ የቦርድ አባላት ፣ የአካደሚክና የአስተዳደር ዘርፍ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች እንዲሁም ከአካባቢው ማህበረሰብ ለተውጣጡ የአማካሪዎች ምክር ቤት አባላትና የአስተዳደር አካላት ነው።

በዚህ ወቅት የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ጫላ ዋታ እንዳሉት ባለፉት ሁለት ዓመታት በዩኒቨርሲቲው ተቋማዊ የሆነ የለውጥ ጉዞ ለማረጋገጥ በተደረገው ርብርብ ተስፋ ሰጪ ውጤት ተገኝቷል።

የ610 ቀናት ልዩ ዕቅድ በማውጣት በመሠረተ ልማት ማስፋፋት፣ በሠላማዊ የመማር ማስተማር፣ በጥናትና ምርምር እንዲሁም በማህበረሰብ አገልግሎት የተሻለ  ውጤት መገኘቱን ጠቅሰዋል።

በተለይ  "ለላቀ ለውጥ እንተጋለን!" በሚል መሪ ሀሳብ በተደረገ ርብርብ መልካም ስም ከመያዝ ባለፈ ለዓለም የዲሞክራሲያዊ አስተዳደር ሥርዓት ተምሳሌት በሆነው የገዳ ሥርዓት ትምህርት በመቅረጽ ከመጀመሪያ እስከ ዶክተሬት ዲግሪ ለመስጠት መቻሉን አስታውቀዋል።

ተቋሙ በፈጣን የልህቀት ጉዞ እንዲገኝ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ የአካባቢው የማኅበረሰብ ተወካዮችና የአስተዳደር አካላት ሚናቸው የላቀ እንደነበረ ጠቅሰው ላበረከቱት አስተዋፅኦ እውቅና መስጠታቸውን ገልጸዋል።

በጋራ በተደረገው ርብርብ ዩኒቨርሲቲው ከነበረበት አስቸጋሪ ሁኔታ ተላቆ በልህቀት ጉዞ ላይ በመድረሱና ሰላማዊ የመማር ማስተማር  ስራ በማረጋገጡ የተሰማቸውን ደስታ የገለጹት ደግሞ በመድረኩ እውቅና ካገኙት መካከል የኃይማኖት መሪ ቄስ በቀለ አኖሌ ናቸው።

በቀጣይም በየደረጃው ካለ የዩኒቨርሲቲው አመራር አካላትና ከአከባቢው ማህበረሰብ ጋር በመቀናጀት የተጀመረው የለውጥ ጉዞ ከዳር እንዲደስ የበኩላቸውን ለመወጣት ቃል ገብተዋል።

ሌላኛው የጉጂ አባ ገዳና የኦሮሚያ አባገዳዎች ምክር ቤት ሰብሳቢ አባ ገዳ ጅሎ ማንዶ በበከላቸው በጋራ በተከናወነው ስራ የመጣውን ለውጥ ከግምት ውስጥ በማስገባት ዩኒቨርስቲው ላዘጋጀው የእውቅናና የምሥጋና መርሃ ግብር አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

በቀጣይም የዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ የትምህርት ዘመኑ ሰላማዊ ሆኖ እንዲሳካ ጠንክሮ እንዲሰራም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም