ለህብረተሰቡ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት አበክሮ እየሰራ መሆኑን ዐቃቤ ህግ ገለጸ

60

ዲላ፣ ጥቅምት 14/2013 (ኢዜአ) በጌዴኦ ዞን የዜጎችን ሰብዓዊ መብት ለማስከበርና ቀልጣፋ የፍትህ አገልግሎት ለመስጠት አበክሮ እየሰራ መሆኑን የዞኑ ዐቃቤ ህግ መምሪያ ገለጸ።

መምሪያው የፍትህ ሥርዓትን ለማሻሻል በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር በዛሬ በዲላ ከተማ መክሯል።

የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪና የዐቃቤ ህግ መምሪያ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ቦኮ በዚህ ወቅት እንዳሉት በዞኑ ፍትህን ለማስፈን የተለያየ ጥረት እየተደረገ ነው።

በተለይ የዜጎችን ሰብዓዊ መብት ከማስከበር አንፃር በፍትህ ተቋማት ከአልግሎት አሰጣጥ ጋር ያሉ ማነቆዎችን በመለየትና በማስተካከል ቀልጣፋ አገልግሎት ለሁሉም ዜጎች በእኩልነት ለማስፈን እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

እስካሁን ከዞን እስከ ቀበሌ ድረስ ባሉ መዋቅሮች የፍትህ ልማት ሠራዊት በመገንባት ሰብዓዊ ጥሰትን የሚቃወም ማህበረሰብ ለመገንባት በተደረገው ጥረት አበረታች ውጤት መገኝቱን ጠቅሰዋል።

በቀጣይም በፍትህ ተቋማት መካከል ተናቦ የመስራት ውስንነትና ውሳኔ ሳያገኙ የሚከባለሉ መዝገቦቶችን እልባት ለመስጠት በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የፍትህ ስርዓቱን የሚያዛቡና የመልካም አስተዳደር ችግር የመሆን አዝማሚያ ያላቸውን ጉዳዮች በፍጥነት በማረም ለህብረተሰቡ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠትና  ሰብዓዊ መብት ለማስከበር ትኩረት ማድረጋቸውን  ገልጸዋል።

የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሽፈራው ቦጋለ በበኩላቸው በፍትህ አገልግሎት አሰጣጥ ረገድ የሚስተዋለው የቅንጅትና የአሰራር ግድፈት በፍጥነት ሊታረም እንገደሚባ አሳስበዋል።

በጉዳዩ ላይ በተከታታይ በግልፅ በመወያየትና በማረም የሚሰጠው የፍትህ አገልግሎት ወቅቱ ወደ ሚጠይቀው መስፈርት ማድረስ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎችም የፍትህ ስርዓትን ለማሻሻል በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ የጋራ መግባባት ላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል።

በዐቃቤ ህግ፣ ፍርድ ቤትና ፖሊስ መካከል የሚስተዋሉ የቅንጅትና የአሰራር ችግሮችን በዘላቂነት በመፍታት ቀልጣፋ የፍትህ አገልግሎት ለህብረተሰቡ ለመስጠት እንደሚጥሩም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም