የመብራት አገልግሎት ከአቅም በላይ ክፍያ እየተጠየቁ መቸገራቸውን በነቀምቴ ደንበኞች ገለጹ

91

ነቀምቴ ፣ ጥቅምት 14/2013 (ኢዜአ) የመብራት አገልግሎት የሚጠየቁት ክፍያ ከአቅም በላይ ሆኖባቸው መቸገራቸውን በነቀምቴ ከተማ ደንበኞች ገለጹ።

ነዋሪዎቹ ለኢዜአ እንዳሉት በኢትዮጵያ መብራት አገልግሎት  የነቀምቴ የአገልግሎት መስጫ ማዕከል  የአገልግሎት ክፍያ  የሚጠይቃቸው በቆጣሪ ንባብ ሳይሆን በግምት ነው።

የከተማው   ነዋሪ የሆኑት አቶ ደበላ በዳሣ  እንደተናገሩት ቆጣሪ ሳይነበብ ወርሃዊ ክፍያ በግምት ከአቅም በላይ የሆነ ከፍተኛ ገንዘብ  እየተጠየቁ ነው፡፡

የቆጣሪ ንባብ ይዘው እንዲመጡ እየተጠየቁ መሆኑንና ይህንን ፈፅመው ቢገኙም ዋጋውን ለማስተመን እስከ አራት ቀናት  በመፍጀት መቸገራቸውን አስረድተዋል።

ከተተመነላቸው በኋላም ለመክፈል ተመሳሳይ ቀናት እንደሚጠብቁ አመልክተዋል።

ሌላው የከተማዋ  ነዋሪ አቶ ሳሙኤል ዘሪሁን በበኩላቸው የደንበኞች አገልግሎት ማዕከሉ ተገልጋዩን ሕዝብ በተገቢው እያገለገለ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

አልፎ አልፎ የቆጣሪ ንባብ ቢኖርም አንባቢዎቹ  የአንዱን ደንበኛ ቆጣሪ ንባብ በሌላኛው ላይ ስለሚመዘግቡ ለከፍተኛ ወጪ መዳረጋቸውና ስህተት ለማረም ፈቃደኛ እንዳልሆኑ አስረድተዋል።

ለአንድ ቆጣሪ 2ሺህ ብር የፍጆታ ክፍያ ተጠይቀው ክፍያውን ከፈፀሙ በኋላ  እንዲታይላቸው ቅሬታ አስገብተው   የ552 ብር እላፊ መኖሩ ከተረጋገጠ በኋላ  እንዲስተካከልላቸው ለስድስት  ወራት ተመላልሰው ቢጠይቁም  ምላሽ ማጣታቸውን ገልጸዋል፡፡

በመኖሪያ ቤታቸው ለመብራት ብቻ የሚገለገሉበትን ቆጣሪ በወር 1ሺህ 889 ብር ተጠይቀው እንዲከፍሉ  መገደዳቸውን የተናገሩት ደግሞ  የከተማዋ ቀበሌ ዘጠኝ   ነዋሪ አቶ ንጉሡ ደጀኔ ናቸው።

የተጠየቁት ክፍያ ያልተገባ መሆኑን ገልጸው ቅሬታ ቢያቀርቡም የሚሰማቸው አካል ባለመኖሩ  ምላሽ ሳያገኙ መቅረታቸውን ገልጸው፣ የአገልግሎት አሰጣጡም እንዳማረራቸው ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ መብራት አገልግሎት የነቀምቴ የደንበኞች አገልግሎት መስጫ ማዕከል የቁጥር አንድ ሥራአስኪያጅ አቶ እምሩ አዱኛ  ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ የቆጣሪ ንባብን  ክፍተት መኖሩን አምነው፣  አሁን ላይ  አሰራሩ ወደ "ጂፒኤስ "በመቀየሩ መሣሪያው ያለውን ውዝፍ ጨምሮ በማንበቡ ምክንያት በደንበኞች ላይ ከፍተኛ ክፍያ መምጣቱን  አስረድተዋል፡፡

ደንበኞች ያለ ምንም መጨናነቅ የሚፈለግባቸውን የአገልግሎት ክፍያ በባንክ በኩል እንዲፈጽሙ መደረጉ ችግሩን የፈታ ቢሆንም ሰሞኑን የሲስተም መበላሸት በመከሰቱ በደንበኞች ላይ መጉላላት እንደደረሰ ተናግረዋል።

አሁን ያለውን ሲስተም በማዘመን  ለደንበኞች የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ መብራት አገልግሎት የነቀምቴ ዲስትሪክት ሥራ አስኪያጅ አቶ ብርሃኑ ኦልጅራ በበኩላቸው ከኔት ወርክ ችግር ጋር በተያያዘ ለደንበኞች የሚፈለገውን አገልግሎት መስጠት እንዳልተቻለ ገልጸዋል።

ሆኖም አሁን ያለውን ሲስተም ወደ "ኦፕቲክ ፋይቤር" በመቀየር  ለደንበኞች ቀልጣፋ አገልግሎትለመስጠት አስፈላጊው ክፍያ ለኢትዮ ቴሌኮም መፈጸሙን ጠቁመዋል።

 የቆጣሪ ንባብን  አሰራሩ ወደ "ጂፒኤስ "ስለተቀየረ ችግሩ  እንደሚፈታ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም