በምዕራብ ጎንደር ለመጀመሪያ ጊዜ የቆላ ስንዴ በመስኖ ለማልማት ዝግጅት እየተደረገ ነው

75

መተማ ጥቅምት 13/2013 (ኢዜአ) በምዕራብ ጎንደር ዞን በ1ሺህ237 ሄክታር መሬት ላይ የቆላ ስንዴ በመስኖ ለማልማት የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡

 ዞኑ ዓመቱን ሙሉ የሚፈሱ ወንዞች፣  ሰፊና ሜዳማ የእርሻ ቦታ ያለበት በመሆኑ ለመስኖ ልማት የተመቸ  መሆኑን ተገልጿል።

በመምሪያው የመስኖና ፍራፍሬ ልማት ባለሙያ   አቶ ጌትነት ካሳሁን እንዳሉት ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም  በምዕራብ አርማጭሆ፣ ቋራና መተማ ወረዳዎች በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ለማልማት ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው።

በዘንድሮ በጋ ለመጀመሪያ ጊዜ በመስኖ በሚካሄደው የስንዴ ልማትም 3ሺህ 940 ወጣቶችና አርሶ አደሮችን ለማሳተፍ  የመለየትና ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ ቀድሞ መከናወኑን አስረድተዋል፡፡

የመስኖ ልማቱን ለማካሄድ የሚያስችሉ እያንዳንዳቸው 100 የፈረስ ጉልበት ያላቸው 13 የውሃ መሳቢያ ጀኔሬተሮች በክልሉ ግብርና ቢሮ ድጋፍ መደረጉንም አመልክተዋል፡፡

ለመስኖ ልማቱ የሚሆን ከ15 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር እንደሚቀርብ ጠቁመው ለመጀመሪያ ጊዜ በሚካሄደው ስንዴ ልማት 410 ሺህ ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን ገልጸዋል።

በመስኖ የሚለማው ስንዴም ከውጭ የሚገባውን ለመተካት በሃገር አቀፍ ደረጃ የተያዘውን ግብ የማሳካት አካል ነው ተብሏል።

በምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ የምድረ ገነት ቀበሌ  አርሶ አደር ተመስገን አያናው በሰጡት አስተያየት  ካላቸው 2 ሄክታር መሬት ውስጥ ግማሹን የአንገረብ ወንዝን ተጠቅመው በመስኖ ሽንኩርት በማምረት ሲጠቀሙ መቆየታቸውን አውስተዋል።

ዘንድሮ ግን አዲስ የመንግስት አቅጣጫ በመምጣቱ ግማሽ ሄክታሩን በሽንኩርት በመሸፈን ቀሪውን   ደግሞ በቆላ ስንዴ ለማልማት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡

"በተደረገልን የግንዛቤ ማስጨበጫ መሰረት በሄክታር ከ40 ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰብ ይቻላል" ያሉት አርሶ አደሩ በልማቱ ውጤታማ ለመሆን ተግተው እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

የምርጥ ዘርና የውሃ መሳቢያ ሞተር በመንግስት በኩል በብድርና ድጋፍ  እንደሚቀርብላቸው እንደተነጋረቸው ጠቅሰው ይህም  የመስኖ ልማቱን ለማቀላጠፍ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርላቸው አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም