የኤርትራ ኤምባሲ በአዲስ አበባ መከፈቱ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ይበልጥ ያጠናክረዋል - የአዲስ አበባ ነዋሪዎች

84
አዲስ አበባ  አምሌ 9/2010 የኤርትራ ኤምባሲ በአዲስ አበባ መከፈቱ የሀገራቱን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከማጠናከሩ ባሻገር የህዝቦችን መቀራረብ ወደ ነበረበት ለመመለስ እንደሚያስችል የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለፁ። በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የተፈጠረውን ጦርነት ተከትሎ ላለፉት 19 ዓመታት ዝግ ሆኖ የቆየው የኤርትራ ኤምባሲ ዛሬ በተከናወነ ደማቅ ስነ-ሰርዓት በታላቅ ድምቀት ዳግም ተከፍቷል። የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በኢትዮጵያ ያደረጉትን ጉብኝት አጠናቀው ወደ አስመራ ከመመለሳቸው በፊት የሀገራቸውን ኤምባሲ ጽህፈት ቤት መርቀው ከፍተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድም በመሃል አዲስ አበባ መስቀል አደባባይ አካባቢ የሚገኘውን የቀድሞ የኤርትራ ኤምባሲ ቁልፍ ለፕሬዚዳንት ኢሳያስ አስረክበዋል። ይህንኑ ክንዋኔ በተመለከተ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት የኤምባሲው ዳግም መከፈት የሁለቱን አገራት ህዝቦች የበለጠ ለማቀራረብ ከፍተኛ ሚና አለው። ከነዋሪዎቹ መካከል ኮለኔል ታምራት ነጋሽ እንደተናገሩት የኤምባሲው መከፈት የሁለቱን አገሮች ግንኙነት የሚያጠናክርና የበለጠ ህዝቦች እንዲቀራረቡ የሚያደርግ ነው፡፡ ለረዥም ጊዜ ተራርቆ የነበረ ህዝብ ወደ አንድነትና ወደ ፍቅርና ሰላም ሲመጣ እንደገናም ደግሞ በኤምባሲ ደረጃ ተከፍቶ ሥራ እንዲጀምር ሲደረግ እጅግ በጣም ጠቃሚና ለወደፊቱም በህብረት ለመኖር የሚያስችል መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ሌላው የአዲስ አበባ ነዋሪ አቶ እሸቱ አሰምሬ ናቸው ሰላም ለሰው ልጅ ከምንም በላይ አስፈላጊ ነው ከዚህ አንጻር በሁለቱ አገሮች መካከል የተጀመረው ግኑኝነት በጣም የሚያስደስት እንደሆነ የተናገረቸው የከተማዋ ነዋሪ መቅደስ ተስፋዬ ይህ ለስደተኞች ተስፋ መሆኑን ጠቅሳ ለዚህ ተግባራቸው ዶክተር አብይ ሊመሰገኑ ይገባል ብላለች፡ የኤርትራ ኤምባሲ በመከፈቱ በጣም ደስተኛ እንደሆነ ከዚህ በኋላ ደግሞ ወደ ኤርትራ  ለሽርሽር እንሄዳለን  አዲስ ዓመትንም ከኤርትራዊያን ጋር እናከብራለን ያለው ደግሞ  የከተማው ነዋሪ ምህረት የህይ ነው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በኢትዮጵያ ለሶስት ቀናት ያደረጉትን ይፋዊ የሥራ ጉብኝት አጠናቀው ረፋዱ ላይ ወደ አስመራ ተመልሰዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም