በ44 የምግብ አምራችና የመድሃኒት አስመጪ ተቋማት ላይ እርምጃ ተወሰደ

85

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13/2013(ኢዜአ) በ44 የምግብ አምራችና የመድሃኒት አስመጪ ተቋማት ላይ እርምጃ መውሰዱን የኢትዮጵያ የምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

ባለስልጣኑ ባሳለፍነው ሶስት ወራት 91 የምግብ ዓይነቶች ደረጃቸውን ያልጠበቁ በመሆናቸው እንዲታገዱና ከገበያ እንዲሰበሰቡ ማድጉንም አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ የምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን የተቋሙን የሶስት ወር ዕቅድ አፈጻጸም አስመልክቶ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ 

የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ አቶ አበራ ደነቀ በዚሁ ወቅት እንዳሉትም በሩብ ዓመቱ ባለስልጣኑ የምግብ እና የመድሃኒት ደህንነትን ከማስጠበቅ አንጻር ሰፊ ስራ ሰርቷል፡፡

በዚህም መሰረት 537 ሺህ ቶን ምግቦች ዓይነቶች ደረጃቸውን የጠበቁ በመሆናቸው ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ መደረጉን አስታውቋል፡፡

ጥራታቸውን ያልጠበቁ እና ወደ አገር ውስጥ ቢገቡ ጉዳት ሊያደርሱ ይችላሉ የተባሉ 24 ነጥብ 2 ቶን በላይ የሚሆኑ የምግብ ዓይነቶች አገር ቤት እንዳይገቡ መደረጋቸውንም ተናግረዋል፡፡

ከቁጥጥር አንጻርም ተቋሙ የተለያዩ ስራዎች ማከናወኑን የገለጹት አቶ አበራ 21 የሚሆኑ የምግብ ድርጅቶች ላይ ከማስጠንቀቂያ እስከ ፈቃድ መቀማት የሚደርስ እርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል፡፡

ድርጅቶቹም የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው ምግቦች ሲሸጡ በመገኘታቸው እና የአሰራር ሂደትን ሳይጠብቁ በማምረታቸው እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

ባሳለፈው ሶስት ወራት 91 የምግብ ዓይነቶች ደረጃቸውን ያልጠበቁ በመሆናቸው እንዲታገዱና ከገበያ እንዲሰበሰቡ መደረጉንም አስታውቋል፡፡

የመድሃኒት ጥራትን ለመቆጣጠር በተሰራው ስራም ጥራታቸውን የጠበቁ ከ4 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው መድሃኒቶች ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ መደረጉን አቶ አበራ ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም የ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ግምት ያላቸው የህክምና መሳሪያዎች ጥራቸው ተረጋግጦ አገር ቤት መግባታቸውን ተናግረዋል፡፡

ከቁጥጥር አንጻርም ተቋሙ 23 የመድሃኒት ተቋማት ከማስጠንቀቂያ እስከ ፈቃድ መቀማት የሚደርስ እርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል፡፡ 

ተቋማቱም ፈዋሽነቱ ያልተረጋገጠ መድሃኒት ይዘው በመገኘታቸው እንዲሁም የጥራት ጉድለት ያለባቸውን ሳኒታይዘሮች እየሸጡ በመገኘታቸው እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡

ህብረተሰቡ መድሃኒት በሚገዛበት ወቅትም የተመዘገበ እና ጥራቱ የተረጋገጠ መሆኑን የሚያረጋግጥበት አይ ቬሪፋይ የተባለ የሞባይል መተግበሪያ አፕሊኬሽን በስራ ላይ መዋሉንም ጠቁመዋል፡፡

ህብረተሰቡም በመድሃኒቱ ላይ ያለውን ቁጥር እና ስም ወደ እዚህ መተግበሪያ በማስገባት መድሃኒቱ ህጋዊ እና ፈዋሽነቱ ተረጋገጠ እንደሆነ ማረጋጋጥ እንደሚችልም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም