በአፍሪካ የአየር ንብረት መረጃ ልውውጥ ስምምነትን ተግባራዊ ለማድረግ ምክክር ተደረገ

127
አዲስ አበባ  ሰኔ 9/2010 በአፍሪካ የአየር ንብረት መረጃ ልውውጥ ስምምነትን ተግባራዊ ለማድረግ ምክክር መደረጉን በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አስታወቀ። የአየር ንብረት መረጃ ልውውጥ በተመለከተ ከአፍሪካ የአየር ንብረት ማዕከላት እና ከብሄራዊ የሜቲዎሮሎጂና የሃይድሮሎጂካል ማዕከላት የተወጣጡ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የሚሰሩ ሳይንቲስቶች የተሳተፉበት አውደ ጥናት በሴኔጋል ዳካር ከተማ ተካሄዷል። ለሁለት ቀናት በተካሄደው አውደ ጥናት ተሳታፊዎቹ በአፍሪካ የአየር ንብረት መረጃን ለማጠናከር አስፈላጊ የሆኑ አቅጣጫዎችን አስቀምጠዋል። አውደ ጥናቱ በአፍሪካ  የአየር ንብረት መረጃ ልውውጥ ለማድረግ የሚያስችለውን 'የዓለም የሜቲዎሮሎጂ ድርጅት ሬዞልሽን 40 ' የተሰኘው ስምምነት አስፈላጊ የሆኑ መመሪያዎችና መስፈርቶች ላይ ያተኮረ መሆኑም ተገልጿል። ስምምነቱ በሰዎች ህይወትና ንብረት ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን ለመከላከል፣ የአየር ንብረትና የአየር ጸባይን ለመተንበይና ለመግለጽ አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችንና ምርቶችን ለማምረትና ለማስተላለፍ ከሚወጣው ወጪ በስተቀር ስምምነቱን የፈረሙ አባል አገራት ነጻና ያልተገደበ መረጃ እንዲያቀርቡ የሚያስችል መሆኑም ተጠቅሷል። በአየር ንብረት መረጃ ልውውጥ ላይ ያሉ ምርጥ ተሞክሮዎችንና ተግዳሮቶችን መለየት፣ የአፍሪካ የአየር ንብረት መረጃ ማዕከላት ደረጃቸውን በጠበቁ መስፈርቶች መሰረት እንዲሰሩ የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን ማስቀመጥ  ከአውደ ጥናቱ ዓላማዎች መካከል ተጠቅሰዋል። በዓለም አቀፍ የሜቲዎሮሎጂ ድርጅት (WMO) አማካሪ ሚስተር ስቴፋን ጆርጅ አውደ ጥናቱ በአፍሪካ የሜቲዎሮሎጂ መረጃ ልውውጡን በዘመናዊና በተደራጀ መንገድ ለማከናወን በጣም አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል። የሴኔጋል የሜቲዎሮሎጂካል ዳይሬክተር ማሪያኔ ዲዮፕ ኬን ተሳታፊዎቹ አውደ ጥናቱ ላይ የተቀመጡት አቅጣጫዎች ተግባራዊ እንዲሆኑ መስራት እንዳለባቸውና ይህም በአፍሪካ የአየር ንብረት አገልግሎት እንዲሻሻል የሚያስችል መሆኑን መናገራቸውም ተገልጿል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም