በጊምቢ የወጣቶች መዝናኛ ማዕከላት አለመኖር ወጣቶች ባልባሌ ቦታ እንዲውሉ እያደረገ ነው

147
ጊምቢ ሀምሌ 9/2010 በጊምቢ ከተማ የወጣቶች መዝናኛ ማዕከላት አለመኖር ወጣቶች ጊዜያቸውን በአልባሌ ቦታ እንዲያሳልፉና ለሱስ እንዲጋለጡ እያደረገ መሆኑን ነዋሪዎች ገለጹ። ኢዜአ ያነጋገራቸው አንዳንድ የጊምቢ ከተማ ነዎሪዎች እንዳሉት በከተማዋ ምንም ዓይነት የወጣቶች መዝናኛ ማዕከል ባለመገንባቱ ወጣቱ ጊዜውን በአልተገባ ቦታ እያሳለፈ ይገኛል። በከተማዋ የቀበሌ 03 ነዋሪ አቶ ባጫ ጉታ እንዳሉት ለወጣቱ መዝናኛ ማዕከል አለመኖር ወጣቶቹን ለተለያዩ ሱሶች ከማጋለጥ ባለፈ ለሕብረተሰቡ ስጋት እየሆኑ እንዲመጡ አድርጓል። ለሱስ የተጋለጡ በርካታ የከተማዋ ወጣቶች ለተስፋ መቁረጥና ለስነ-ልቦና ቀውስ በመዳረግ የአፍላ ወጣትነት ጊዜያቸውን በከንቱ በማባከን ላይ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ አቶ መኮንን ዲነግዴ የተባሉ የከተማዋ ነዋሪ ናቸው። ወጣት ማሞ ያደታ በበኩሉ ከአስር ዓመት በፊት በከተማዋ ማዕከላዊ ቦታ የወጣቶች ሁለገብ መዝናኛ ማዕከል ይገነባል ተብሎ የመሰረተ ድንጋይ ቢቀመጥም እስካሁን ድረስ እውን አለመሆኑን ነው የገለጸው። "በዚህ ምክንያት እርሱን ጨምሮ በርካታ የከተማዋ ወጣቶች የሚውሉበት ቦታ በማጣት ባልተገባና ለሱስ በሚያጋልጡ ስፍራዎች ጊዜያቸውን በማባከን ለጉዳት እየተዳረጉ ናቸው" ብሏል። እንደ ወጣቱ ገለጻ እርሱን ጨምሮ በአካባቢው የሚያውቃቸው ሌሎች ወጣቶች ለሲጋራ፣ ለመጠጥና ለተለያዩ ሱሶች ተጋልጠው ይገኛሉ። ሌላኛው የከተማዋ ወጣት ሚፍታህ ሙሳ በበኩሉ " ጥቂት የማይባሉ የከተማዋ ወጣቶች በመንገድ ዳር ጫት እየቃሙና ሲጋራ እያጨሱ ከመዋል ባለፈ ለሱሳቸው ከቤተሰባቸው ገንዘብ በጉልበት ሲቀበሉ ታዝቢያለሁ" ብሏል። አንዳንዴም ገንዘብ ሲያጡም የስርቆት ወንጀል በመፈጸም በሕብረተሰቡ ላይ ስጋት እየፈጠሩ በመሆኑ የሚመለከተው አካል ከወዲሁ መፍትሄ ሊያበጅ እንደሚገባ አመልክተዋል። የጊምቢ ከተማ የወጣቶችና ስፖርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጋዲሳ ኩመራ በበኩላቸው በማምርት ዕድሜ ክልል የሚገኙ በርካታ ወጣቶች ጊዜያቸውን በአልባሌ ቦታ እያሳለፉ መሆኑን ገልጸዋል። "ከአስር ዓመት በፊት በኦሮሚያ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ለመገንባት የታቀደው የወጣቶች ማዘውተሪያ ማዕከል እስካሁን ተግባራዊ ባለመደረጉ ወጣቱ መዝናኛ ቦታ በማጣት በቀላሉ ለሱስ ተገዥ እየሆነ  ነው" ብለዋል። ቢሮው የበጀት እጥረት እንዳጋጠመውና ሥራውም ከከተማው አስተዳደር አቅም በላይ መሆኑ ማዕከሉ ሳይሰራ እንዲቆይ ማድረጉን በምክንያትነት ጠቅሰዋል። የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት በ2011 በጀት ዓመት በ10 ሚሊዮን ብር የወጣቶች መዝናኛ ማዕከል ለመገንባት መታቀዱንኝ አቶ ጋዲሳ አመልክተዋል። ወጣቶቹ ለሱስ ተጋላጭ ከሚያደርጓቸው አካባቢ በመራቅ በከተማው የህዝብ ቤተ መጻህፍት ተጠቅመው እውቀት እንዲገበዩ በተገኘው መድረክ ሁሉ ጥረት ቢደረግም እምብዛም አለመሳካቱን ነው የገለጹት። ወጣቱም ማዕከሉ ተገንብቶ ለአገልግሎት እስኪበቃ ድረስ  ወጣቶች  በተለያዩ የመዝናኛ አማራጮች በመጠቀም እራሳቸውን ከሱስ እንዲጠብቁ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም