በአፍሪካ የኮቪድ- 19 ወረርሽኝን ለመግታት ፈጣን የምርመራ ሂደት ተጠናክሮ ይቀጥላል

592

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12(ኢዜአ) በአፍሪካ ያለውን የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ፈጣን ምርመራ ለማሳደግ የሚያግዝ በኢንተርኔት የታገዘ ውይይት ዛሬ ተካሄዷል፡፡

በውይይቱ ላይ በአፍሪካ የኮቪድ -19 ወረርሽኝን ለመግታት የተጀመረው የፈጣን ምርመራ አተገባበር የሚደነቅ መሆኑን በአለም ጤና ድርጀት የአፍሪካ ተጠሪ ማቲስዲስሞ ሞቲ ተናግረዋል፡፡

በምርመራ ሂደቱ ወደ ኋላ የቀሩ አገራትን በመለየት የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የተጠናከረ ጥረት እንደሚደረግም ገልጸዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የታደሙት የጊኒ፣ የኡጋንዳና ሴኔጋል ተወካዮች በአገራቸው ያለውን ተሞክሮ አካፍለዋል፡፡

በአፍሪካ ሴኔጋልና ናይጀሪያ ፈጣን ምርመራ በማድረግ የተሻለ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ተጠሪዋ ጠቁመዋል፡፡

አህጉሪቱ በተጨናነቀ ሁኔታ የሚኖሩ በርካታ ዜጎች የሚገኙባት መሆኑ ወረርሽኙን አስጊ አድርጎታልም ብለዋል፡፡

የዓለም ጤና ድርጀት ወረርሽኙን ለመግታት የሚያግዙ የፖሊሲ አተገባበር መመሪያዎችንና ግብዓቶችን በመላክ ከፍ ያለ እገዛ እያደረገ እንደሚገኝም አስታውቀዋል፡፡

በአፍሪካ በኮቪድ -19 አሁን ላይ 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሰዎች የተያዙ ሲሆን የ40 ሺህ 400 ሰዎች ህይወትም አልፏል።

የወረርሽኙ ምጣኔ በሰሜን አፍሪካ ጎልቶ የሚታይ ቢሆንም አሁን ላይ ምጣኔው በመቀነስ ላይ ይገኛል ተብሏል።

ወረርሽኙን ለመከላከል ሁላችንም ማስክ ማድረግ፣ ርቀታችንን መጠበቅና እጃችንን በተደጋጋሚ መታጠብ አለብን ሲሉ አሳስበዋል፡፡

በአፍሪካ የሚከናወነው ምርመራ ከሌሎች አህጉራት አንጻር ዝቅተኛ በመሆኑ በቁጥሩ መዘናጋት እንደማይገባም ኃላፊዋ አስገንዝበዋል፡፡

ለአገራት የሚደረገው የመመርመሪያ ግብዓት አቅርቦት ተጠናከሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል፡፡

ለወረርሽኙ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት በሚደረገው ጥረት በገበያ ላይ የሚታየው የግብዓት አቅርቦት ሰንሰለት መበላሸት ተግዳሮት እንደሆነባቸውም ተጠሪዋ ገልጸዋል፡፡

አሁን ላይ ለአገራቱ በምናደርገው የግብዓት አቅርቦት የገጠመንን ፈተና ለማለፍ ከፍተኛ ጥረት ይጠይቀናል ብለዋል፡፡

አፍሪካ ከዚህ ወረርሽኝ ልምድ በመውሰድ በቀጣይ ሊገጥማት የሚችለውን ወረርሸኝን ለመቋቋም መዘጋጀት አለባት ሲሉም አሳስበዋል፡፡

ለዚህ ስኬት ደግሞ አገራት፣ የግል ተቋማት፣ ታዋቂ ግለሰቦችና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በጋራ መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

የኮቪድ -19 ወረርሽኝ በአፍሪካ በቀጣይ ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ የቅድመ ጥንቃቄ እርምጃዎችን አጠናክረን መተግበር አለብን ሲሉ አሳስበዋል፡፡