በአሥር ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ ለአካል ጉዳተኞች ተጠቃሚነት ትኩረት ይደረጋል--- የፕላንና ልማት ኮሚሽን - ኢዜአ አማርኛ
በአሥር ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ ለአካል ጉዳተኞች ተጠቃሚነት ትኩረት ይደረጋል--- የፕላንና ልማት ኮሚሽን
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12/2013 (ኢዜአ) በአሥር ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ ለአካል ጉዳተኞች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ትኩረት የሚደረግ መሆኑን የፕላንና ልማት ኮሚሽን ገለጸ።
በፕላንና ልማት ኮሚሽን የአሥር ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ ላይ ከተለያዩ የአካል ጉዳተኞች ማኅበራት ከተውጣጡ አካላት ጋር ኮሚሽኑ ውይይት አድርጓል።
የፕላንና ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነሯ ዶክተር ፍጹም አሰፋ በሰጡት ማብራሪያ መሪ ዕቅዱ ለአካል ጉዳተኞች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ትኩረት አድርጓል ብለዋል።
የተቋማት የአሥር ዓመት መሪ የልማት ዕቅዳቸውም የአካል ጉዳተኞችን ፍትሐዊ ተጠቃሚነትና አካታችነት ያገናዘበ ስለመሆኑም ገልጸዋል።
በቀጣይም አስቻይ የሆኑ የሕግ ማዕቀፎችን በማዘጋጀት ወጥነት ያለው ተቋማዊ አሠራር መዘርጋት የግድ መሆኑን አብራርተዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በአካል ጉዳተኞች ዙሪያ በየወቅቱ የሚወጡ ሕጎችና መመሪያዎች ቢኖሩም ተፈጻሚነታቸው ግን እምብዛም ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማኅበር ዋና ዳይሬክተር አባይነህ ጉጆ፤ መሪ ዕቅዱ የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ያካተተ በመሆኑ አመስግነዋል።
ቀደም ሲል በአካል ጉዳተኞች ዙሪያ የወጡ አስገዳጅ ሕጎች፣ መመሪያዎችና አዋጆች ቢኖሩም ተፈጻሚነት ላይ ክፍተቶች መኖራቸውን ጠቅሰው በቀጣይ ይህ እንዳይሆን ጠይቀዋል።
የአካል ጉዳተኞች የሕንፃ አዋጅ በሥራ ላይ እየዋለ ቢሆንም በሚፈለገው ልክ አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ እያደረገ አለመሆኑን ጠቅሰው ይህም በድጋሚ ሊፈተሽ ይገባል ብለዋል።
አካል ጉዳተኞችን በቀጥታ የሚመለከቱ ሕጎች ሲደነገጉ ማኅበሩን በማማከር ቢሆን የተሻለ ይሆናልም ሲሉ ተናግረዋል።
አሁንም ተቋማት የሚያቅዱት ዕቅድ ላይ የአካል ጉዳተኞች አካታችነትን በሚመለከት በቅርበት ሊወያዩ እንደሚገባ ገልጸዋል።
አቶ ሚስባህ መሀመድ የተባሉ የውይይቱ ተሳታፊ በበኩላቸው አካል ጉዳተኞች የሥራ ዕድል በማግኘት ላይ ብዙ ማነቆዎች እንዳሉ ጠቁመዋል።
በፖለቲካ በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይም እንዲሁ ከፍትሐዊ ተጠቃሚነት አንፃር የሚታዩ ጉድለቶች አሉ ብለዋል።
የፕላንና ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነሯ ዶክተር ፍጹም በሰጡት ማብራሪያ በቀጣዮቹ አሥር ዓመታት የኢትዮጵያን አማካይ ዕድገት ከ10 በመቶ በላይ ከፍ ለማድረግ ይሠራል ብለዋል።
በ2020 ዓ.ም ኢትዮጵያን በዕድገትና ልማት "አፍሪካዊ ተምሣሌት" ለማድረግ መታቀዱንም ገልጸዋል።
በድህነት ቅነሳ ዙሪያ ከነበረበት 30 በመቶ ወደ 19 በመቶ ዝቅ ማድረግ ቢቻልም በቀጣይ ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል።
በነዚህ እንቅስቃሴዎች ሁሉ ግን የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎና ተጠቃሚነት ግድ ስለመሆኑ አረጋግጠዋል።
በኢትዮጵያ አሁን ላይ ከ20 ሚሊዮን በላይ አካል ጉዳተኞች እንዳሉ መረጃዎች ያመለክታሉ።